አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015( ኤፍ ቢ ሲ) “ሮሴቲ” የተሠኘው የሩሲያ የትራንስፎርመር እና የኤሌክትሪክ ገመድ አምራች ኩባንያ በዘርፉ ከተሰማሩ የኢትዮጵያ ባለሐብቶች ጋር መሥራት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡
የኢፌዴሪ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሐብታሙ ኢተፋ በትብብር ለመሥራት ከሩሲያ “ሮሴቲ” ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን ልዑካን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ÷ ኢትዮጵያ ለማኅበረሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ የምታደርገውን ርብርብ በማገዝ ረገድ የሩሲያው “ሮሴቲ ኩባንያ” ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ነው የጠቆሙት፡፡
በዚህም ኩባንያው ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ፍላጎት በማሳየቱም ደስተኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አማካሪ አሌክሳንደር ኮምሳሮቭ ፥ ኩባንያው በዘርፉ ከሀገር ውስጥ የግል ባለሐብቶች ጋር ሆኖ ለመሥራት የሚያደርገውን ጥረት ሚኒስቴሩ እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡