Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለመከላከያ ሠራዊት ከ42 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ42 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ አስረክበዋል፡፡

ወይዘሮ ዳግማዊት በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ድጋፉ የሰላም አማራጭን አሻፈረኝ ብሎ አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ውጊያ የመከላከል ርምጃ እየወሰደ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነታችንን ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት መሰል ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን የጠቀሱት ሚኒስትሯ÷ በቀጣይም ተቋሙ ተጨማሪ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የገንዘብና የአይነት ድጋፉን የተረከቡት ወይዘሮ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፥  ተቋማቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

ከገንዘብ እና ከዓይነት ድጋፉ በተጨማሪ የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ደም መለገሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ደም ለጋሾቹ ህይወት ለሚሰጠው መከላከያ ሰራዊት የሚተካውን ደማችንን መለገሳችን ትንሹ ስጦታ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ከደም ልገሳና ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በማንኛውም መልኩ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ደጀንነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

Exit mobile version