አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዶክተር ካትሪን ሐምሊን ሕልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ።
በኢትዮጵያ የፌስቱላ ህክምና መስራች የነበሩት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በ96 ዓመታቸው በትናንትናው እለት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት፥ “በዶክተር ካትሪን ሐምሊን ሕልፈተ ሕይወት ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶኛል” ብለዋል።
“ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ከ60 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ክብራቸው የተነጠቀባቸውን በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ዳግም ቀና ብለው እንዲራመዱ ለፍተዋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
እኒህን ብርቅዬ ጌጥ ኢትዮጵያ አጥታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ ለሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ፤ ነፍሳቸው በሰላም ትረፍ” ብለዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሐምሊን የፌስቱላ ሆስፒታል እና የካትሪን ሐምሊን የፌስቱላ ፋውንዴሽን መስራች የሆኑት በዶክተር ካትሪን ሐምሊን ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
ዶክተር ካትሪን ሀምሊን ለኢትዮጵያ ከመቃብር በላይ የሚውል ታሪክን ሰርተው አልፈዋል ያለው የከተማ አስተዳደሩ፥ ለዶክተር ሀምሊን ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ተመኝቷል።