Fana: At a Speed of Life!

የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌቱ የመሳላ በዓል እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት የሆነው የመሳላ በዓል በከንባታ፣ጠንባሮና ዶንጋ ብሔረሰቦች ዘንድ እየተከበረ ነው፡፡

በዓሉ በከንባታ ጠንባሮ ዞን በሚገኙ ሦስት ብሔረሰቦች ማለትም በከንባታ፣ ጠንባሮና ዶንጋ ብሄረሰቦች ዘንድ ነው በየዓመቱ የሚከበረው ፡፡

የመሳላ በዓል በብሔረሰቦቹ  የአዲስ ዓመት መቀበያ ብቻ ሳይሆን አንድነት ፍቅርና መልካምነት የሚታይበት ነው።

በበዓሉ ጊዜ የብሔረሰቦቹ ተወላጅም ቢሆን ከሌላ ቦታ በእንግድነት የመጣ ፤  የሌለው ያለውን ተካፍሎ በደስታ የሚያሳልፍበት ቀን ነው።

የከንባታ ጠንበሮ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አደሮ እንዳሉት ፥ ይህን የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት የሆነውን የመሳላ በዓል ለትውልድ ለማስተላለፍ ከክልል እስከ ፌዴራል መንግስት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ አጪሶ ፥ የከንባታ ማንነት መገለጫ የሆነውን መሳላን ለዓለም ለማስተዋወቅ ዞኑ የአቅሙን ሁሉ ጥረት እያደረገ ቢሆንም በሚጠበቀው ልክ ለዓለም ማስተዋወቅ ግን አልቻልምና ገና ብዙ ስራ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የሀምበሪቾ ሰባት ሳባ ሰባትን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን በየዓመቱ የሚገበኙ ሰዎች እየጨመሩ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ዋና አስተዳዳሪው ፥ በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ300 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ወደዞኑ መምጣታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዴላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው ፥ ባህሉ ለትውልድ እንዲተላለፍ  የሚደረገው ጥረት መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልልም ለዚህ ዓላማ የሚያስፈልገውን ሁሉ  ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት።

በጥላሁን ይልማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.