ኮሮናቫይረስ

ኳራንቲን ምንድነው?

By Tibebu Kebede

March 18, 2020

ከባለፈው ዜና የሰማነው አንድ በኮሮና ቫይረስ ህመም ተጠርጥሮ ወደ ለይቶ ማቆያና ህክምና ተቋም በሚወሰድበት ሰዓት አምልጦ የተለያየ ቦታ ከደረሰ በኋላ ተይዞ ምርመራ ሲደረግለት ነጻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ይህ ስለ ለይቶ ማቆያ በቂ ያልሆነና የተዛባ መረጃ መድረስ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር መደናበር የሚከሰት ስለሆነ እናም በማህበረሰቡ ዘንድ ስለልየታ ማዕከላት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ትንሽ ስለኳራንቲንና ለተላላፊ በሽታዎች ያለው ጥቅም ትንሽ ብናወራ ብዬ አሰብኩ፥

ኳራንቲን ምንድነው?

ኳራንቲን/Quarantine ማለት በአንድ አካባቢ መለየትና እንቅስቃሴ መገደብ ማለት ሲሆን፥ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ ሰው የሚለየው በተከሰተው ተላላፊ በሽታ የመያዝ እድል አጋጥሞት ከነበረ ማለትም የቅርብ ግንኙነት ወይም በሽታው ወደ ተነሳባቸው አካባቢዎች ተጉዞ ከነበረ ወይም ደግሞ የህመሙ ምልክት አሳይቶ በእነዚህ ምክንያቶች በሽታው ሊኖርበት ይችላል ተብሎ ከተጠረጠረ ከማህበረሰቡ እንዲለይ በማድረግ አስፈላጊው ምርመራና ክትትል ይደረግለታል፡፡

የዚህ ዋነኛ አላማ አንድን ተላላፊ ህመም ከአንድ ሰው ወደሌላ ሳይታወቅ እየተዛመተ ለመቆጣጠር እንዳያስቸግርና ለጤና ማዕከላት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ያደርገዋል፡፡

አንድ ሰው በየት ቦታዎች ሊለይ ይችላል?

1. በለይቶ ማቆያና ህክምና መስጫ የተዘጋጁ ማዕከላት ውስጥ ( ለምሳሌ፦የየካ ኮተቤ ልየታ ማዕከል)

በነዚህ ማዕከላት ውስጥ በህመም መከላከልና ማከም የሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚገኙበት ሆኖ አንድ በህመሙ የተጠረጠረ ሰው የበሽታው መኖርና አለመኖር ምርመራ ይደረግለታል፤ ወይም በሽታው ምልክት እስኪያሳይ ድረስ ( በኮሮና ፡ ለ 14 ቀን) እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

በተጨማሪም የህመሙ ምልክት ካለበትና ከተረጋገጠ ደግሞ አስፈላጊው የህክምና ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፡፡ ይህም ፈሳሽ መስጠት፣ የኦክስጅንና ሌሎች መድሃኒቶች ድጋፍ የሚያስፈልግ ከሆነም እሱን በመስጠት ከህመሙ እስኪያገግም ድረስ ክትትል ይደረግለታል፡፡

ከህመሙ ነጻ ሆኖ የተገኘ ሰው ደግሞ ከለይቶ ማቆያው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡

2. መኖሪያ ቤት ወይም መኪና ውስጥ

አንድ ሰው በራሱ በበሽታው የመያዝ ቀጥተኛ አጋጣሚ አለኝ ብሎ ካመነ ራሱን ከቤተሰብ በመለየት በቤት ውስጥ ለይቶ ማስቀመጥ ይችላል፤ ይህም ህመሙ እንደሌለበት እስኪረጋገጥበት ድረስ ማለት መዛመቱን ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን የህመም ምልክት ካለ አስፈላጊው የህክምና ድጋፍ ስለሚያስፈልግ ወደጤና ቦታ ማቅናት ያስፈልጋል፡፡

ካራንቲንና ፍርሃት

ኳራቲን ለተላላፊ ህመሞች ቁጥጥር ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ሆኖ ወደልየታ ማዕከል የሚገቡና የሚወጡ ሰዎች ላይ የፍርሃት የመጨነቅ እንዲሁም የመደንገጥ ስሜትን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህ የታወቀ ሲሆን እያንዳንዱ ሰው በአላስፈላጊ ምክንያት ወደ ልየታ ማዕከል እንዳይገባ፤ የገባም ሰው ደግሞ ከሚያስፈልገው የጊዜ ገደብ በላይ እንዳይቆይ አስፈላጊው ጥንቃቄዎች በህክምና ባለሙያዎችና ልየታ ማዕከላት ተግባራዊ መደረግ አለባቸው፡፡

ከዚያ ባሻገር እኛ እያንዳንዳችን የበሽታውን መዛመት ለመቀነስ ሃላፊነት ወስደን አስፈላጊ የሆኑትን ጥንቃቄዎች ማድረግ መርሳት የለብንም።

በዶ/ር ሮቤል ተድላ