Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአንዳንድ የሀገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ውርጭ ሊከሰት ይችላል- ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው የበጋ ወቅት በአንዳንድ የሰሜን ምሥራቅ፣ ምሥራቅ እና መካከለኛው የሀገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ላይ ውርጭ ሊከሰት እንደሚችል ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ለመጪው የበጋ ወቅት በተሰጠው ትንበያ መሠረት÷ መጪው በጋ በትሮፒካል ፓሲፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛው በታች መቀዝቀዝ እንዲሁም ሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ Negative IOD ስር ሊቆይ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በዚህም በተለይም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑ የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረውና በአብዛኛው በደረቃማ የአየር ጠባይ ተጽዕኖ ሥር እንደሚቆዩ ተጠቁሟል።

እንዲሁም የምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንዲሁም የሰሜን ምሥራቅ፣ የመካከለኛውና የምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ በትንበያው ተመላክቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ÷ የሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅ፣ መካከለኛውና የምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝንባቸው የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚጨምር የሚጠበቅ ሲሆን÷ በአንዳንድ የሰሜን ምሥራቅ፣ ምሥራቅና መካከለኛው የሀገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ላይ ውርጭ እንደሚከሰት ተጠቁሟል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version