አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ ቁርጥራጭ ብረቶችና ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ለብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሽያጭ እንዲተላለፉ መንግስት ወሰነ፡፡
እንደየብረት አይነቶችና የገበያው ሁኔታ የመሽጫ ዋጋ የተዘጋጀ ሲሆን ፥ ይህም የብረት አምራች ፋብሪካዎች ላይ ያለውን የግብዓት እጥረት በከፍተኛ መጠን የሚያቃልል ነው ተብሏል።
ስለሆነም ቁርጥራጭ ብረቶችና ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ፋብሪካዎቹ ያለ ጨረታ በመነሻ ዋጋ እንዲወስዱ በተወሰነው መሰረት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ባገናዘበ መልኩ ድልድል እንደሚካሄድም ነው የተገለጸው።
በዚህም ከፌደራል መስሪያ ቤቶች ፣ ተጠሪ ተቋማት ፣ በፌዴራል ደረጃ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ቁርጥራጭ ብረቶችና ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ለብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሽያጭ ይተላለፋሉ ተብሏል፡፡
በድልድሉ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!