Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ልምድ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደሚያስፋፋ ተመድ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አረንጓዴ አሻራ የቀጠናው አገራት አንድ የትብብር መስክ እንዲሆን ኢትዮጵያ እየሰራች መሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።

 

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ስራ እና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎቿን ያካፈለችበት ውይይት በኒውዮርክ ተካሂዷል።

 

ከ77ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግስት ከመንግስታቱ ድርጅት የልማት ኘሮግራም ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ንግግር አድርገዋል ።

 

አቶ ደመቀ በንግግራቸው የአለም አየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ልማት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት መደቀኑን ገልፀዋል።

 

በከተማ እና በገጠር የሰዎች ፍለሰስት እንዲባባስ ማድጉንም ነው የጠቀሱት።

 

ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሰት ፓሊሲ እና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ በሁሉም ደረጃ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን አስተባብሮ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል እና የማጣጣም ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

 

ግላስኮ ላይ ተካሂዶ በነበረው 26ኛው የአለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ እ.ኤ.አ እስከ 2030 የደን ምንጣሮ እና የመሬት መራቆትን ለመቀልበስ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ኢትዮጵያ 22 ሚሊየን ሄክታር የተራቆተ መሬትን እንዲያገግም ለማድረግ እንዲሁም የደን እና የብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ ቃል በገባችው መሰረት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

 

አለምአቀፉን የአየርንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2019 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን አቶ ደመቀ በመድረኩ በአብነት አንስተዋል ።

 

በመርሃግብሩ 20 ሚሊየን ህዝብን በማሳተፍ ባለፉት አራት አመታት ከ25 ቢሊየን በላይ የዛፍ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።

 

አረንጓዴ አሻራ የቀጠናው ሃገራት አንድ የትብብር መስክ መሆን እንዳለበት ያመለከቱት አቶ ደመቀ ፥ ” አለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ በመከላከሉ ረገድ የቀጠናው ሃገራትን ትብብር ለማጠናከር ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነትን ወደ ጎረቤት ሃገራት ለማስፋት ጭምር እየሰራች ነው ” ብለዋል።

 

ባለፈው አመትም በጎረቤት ሃገራት የዛፍ ችግኞች እንዲተከሉ መደረጉን አስተውሰው በተመሳሳይ በተያዘው አመትም እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በኢኒሼቲቩ የተቀመጡ አላማዎችን ለማሳካት ከአለምአቀፍ እና ቀጠናዊ ከሆኑ አጋር አካላት ጋር ኢትዮጵያ በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥልም አቶ ደመቀ አመልክተው፥ የልማት አጋሮች ኢንሼቲቩን ኢንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የመንግሰታቱ ድርጅት የልማት ኘሮግራም የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት አሁና ኢዛኮኑዋ በተወካያቸው በኩል ባደረጉት ንግግር የአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ የእስካሁን ስኬት ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት እቅዶችን በተሳካ ሁኔታ የመፈፀም አቅሟ ከፍ ያለ ደረጃ መድረሱን ያመላከተ ነው ብለዋል።

 

ዘላቂነት ያለው የአረንጓዴ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ በኢትዮጵያ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች አለምአቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ለሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ሆኖ መወሰድ አለበትም ብለዋል።

 

ተመድ ይህን ተሞክሮንም ወደ 10 የአፍሪካ ሀገራት እንደሚያስፋፋ ነው ያመለከቱት።

 

ሌላው በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአረንጎዴ አሻራ ኢንሼቲቭ ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶ/ር አደፍርስ ወርቁ መርሃግብሩ አዳዲስ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

Exit mobile version