UKRAINE-CRISIS/UN

ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ጎሳዎች መብት ትደፈጥጣለች በሚል የቀረበባትን ውንጀላ ውድቅ አደረገች

By Alemayehu Geremew

September 22, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ጎሳዎቿን መብት ትደፈጥጣለች በሚል በአሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና አውሮፓ ኅብረት የቀረበባትን ውንጀላ ውድቅ አደረገች፡፡

በተመድ የቻይና ቋሚ ተወካይ ዣንግ ጁን ÷ የሀገራቱን ውንጀላ ውድቅ ያደረጉት በተመድ 77ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡

ዣንግ ጁን ÷ ቻይና 56 ጎሳዎች አንድ ሆነው ለጋራ ብልፅግና በኅብር ተሥፋ ሰንቀው የሚኖሩባት ሀገር ናትም ብለዋል፡፡

ቻይና የጋራ ኅልውና ያለው ማኅበረሰብ ግንባታን የሚሹ ጎሳዎች ያሉባት አንድ ሀገር ናት ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

“እንዳለመታደል ሆኖ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች እውነታውን በቸልታ በማለፍ የጠቅላላ ጉባዔውን መንፈስ በቻይና ጉዳይ ላይ ክርክር እና መሠረ- ቢስ ውንጀላ በማቅረብ አሳልፈዋል” ም ነው ያሉት፡፡

ይህንንም ቻይና በፅኑ የምትቃወመው እና ውንጀላውን የማትቀበለው መሆኑን አስታውቃለሁ ብለዋል፡፡

ዣንግ ጁን ÷አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጎሳዎች በዘረኝነት፣ አድልዎ፣ ጥላቻ፣ ጥቃትና በመሳሰሉት ፈተናዎች ሲጠቁ መቆየታቸውን ያልሸሸጉ ሲሆን በተመድ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ችግሩን ለመፍታት ላለፉት 3 አሥርት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ምንም ጥረት እንዳልተደረገ በጉዳዩ ላይ በደፈናው መወንጀል አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ጉባዔው በቁጥር አነስተኛ በሆኑ ብሔሮች ወይም ጎሳዎች እንዲሁም ሃይማኖቶች እና ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን መብት የደነገገው መግለጫ የወጣበትን 30ኛ ዓመት አስቦ ውሏል፡፡