አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኒውዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ ጋር መክረዋል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ወዳጅነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸውና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት በንግድ እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ በትብብር መሥራት የሚያስችል ዐቅም እንዳላቸው እና ግንኙነታቸውንም ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዓለም አቀፍ አጋርነት ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር መክረዋል።
በዚህ ወቅትም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት የማደስ ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል።
ኡርፒላይነን በበኩላቸው የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፥ በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለመደገፍ ያለውን ዝግጁነትም ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ባደረጉት ውይይት ደግሞ ኮሚቴው በኢትዮጵያ በሚያከናወናቸው ተግባራት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ መስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።