Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡት መግለጫ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ያዘለ ነው – በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡት መግለጫ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ያዘለ መሆኑን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ባለፈው ነሐሴ ወር የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ኤምባሲው ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በግጭት ስም ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎችን ለማጣራት እና ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ቁርጠኛ እንደሆነ መግለጹን አስታውሷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ይህን የሚከታተልና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች እና በተመድ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ያደረጉትን ምርመራ ተከትሎ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን የሚተገብር የጋራ ግብረ ኃይል መቋቋሙንም ነው ያስታወሰው።

ግብረ ኃይሉም በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተሳተፉ አካላትን ለህግ የማቅረብ ሃላፊነት መውሰዱን በመጥቀስ፥ ይህን ለማሳከት እንዲረዳው አስፈላጊ እርምጃዎች መውሰዱንም ጠቅሷል።

ይሁን እንጅ የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ይህን በሚጻረር መልኩ በኢትዮጵያ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራና ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉን አንስቷል።

መንግስትም ይህ ውሳኔ ምክር ቤቱ የራሱን ፖለቲካዊ ጫና ለማሳረፍ የሚጠቀምበት መሳሪያ ነው በሚል መቃወሙን በማንሳት፥ ምክር ቤቱ እየተደረገ ላለው ጥረት እውቅና መስጠት እንጅ ማጣጣሉ ተገቢ እንዳልሆነም በመግለጫው አስገንዝቧል።

 

አያይዞም መንግስት ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ለመፍታት ከምክር ቤቱ እና ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር ለመሥራት ሲያደርግ የነበረውን ጥረት ለአፍታም እንዳላቆመ በመግለጫው ያስታወሰው።

መንግስት ይህን እርምጃ የወሰደው ኮሚሽኑን ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መሆኑን እያወቀ ነው ያለው ኤምባሲው፥ መንግስት ሁኔታዎችን ለማጥራት እና በትብብር ለመሥራት በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ጄኔቫ ልኮ እንደነበርም ነው ያስታወሰው፡፡

ልዑኩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከኮሚሽኑ አባላት ጋር መገናኘቱን ያነሳው መግለጫው፥ ከሐምሌ 25 እስከ ሐምሌ 29 ቀን 2022 ድረስ መንግስት የኮሚሽኑን አባላት በአዲስ አበባ ማስተናገዱንም አትቷል።

ከዚህ ባለፈም የተመድን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጨምሮ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጥምረት የምርመራ ሥራዎችን አካሂደው ተቀባይነት ያላቸውን ዘዴዎች ለመፈተሽ ሞክረዋልም ብሏል።

በሁሉም ስብሰባዎች በኢሰመኮ እና የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባልዳሰሷቸው ጉዳዮች ላይ ተኩረቱን ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆነ በትብብር ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ገልጾ እንደነበርም አውስቷል።

ኮሚሽኑ በቅርቡ ያወጣው ሪፖርትም የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወስድ  የሚያበረታታ እና ኮሚሽኑም ከተቋቋመበት አላማ ውጭ ፖለቲካዊ ፍላጎቱን ሠለማስፈጸም ፍላጎት እንዳላው ያሳየ መሆኑንም ኤምባሲው አብራርቷል፡፡

ይህም የኮሚሽኑ ምርመራ ዋና አላማ እና መነሻ ሰብዓዊነት ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት ማጽፈጸሚያ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብሏል፡፡

ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀውን የሰብአዊ ተኩስ አቁም አሸባሪው ህወሓት መጣሱን እንደማያነሳ የጠቆመው መግለጫው፥ ኮሚሽኑ ተዓማኒ እና ትክክለኛ ባልሆነ መረጃ በመመስረት መንግስትን የመወንጀል ሞራል እንደሌለው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ኮሚሽኑ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ያቀረበው መሰረት ቢስ ጥሪም የተቋሙን ግዴለሽነት የሚያሳይ ነው ያለው መግለጫው፥ ከሚሽኑ የሰብዓዊ መብትን ለፖለቲካ ማስፈጸሚያነት ተጠቅሟል፤ ይህም የተቋሙን እውነተኛ ባህሪ ያሳየ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡትን ሪፖርት እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብቶችን እንደሚያከብር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራም በመግለጫው አረጋግጧል።

መንግስት ኢትዮጵያን ማሳፈር አላማው ባደረገና ሃላፊነት በማይሰማው አካል የሀገር ሉዓላዊነት እንዲደፈር አይፈቅድም ያለው ኤምባሲው፥ አጋሮችም የኮሚሽኑን ሃላፊነት በዚህ አመት እንዲያቋርጡና በኮሚሽኑ ሳቢያ የሚደርሰውን ጥፋት እንዲከላከሉም ጥሪውን አቅርቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version