አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በትምህርቱ ዘርፍ የሚታዩ የሙስናና ብልሹ አሠራርን በተመለከተ ጥናት ማካሄዱን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከ600 በላይ ለሚሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ የትምህርት ዘርፍ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ሥራ አስፈፃሚዎች በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
በስልጠናው ላይ ኮሚሽኑ ያስጠናው በትምህርት ሴክተሩ የሚታዩ የሙስና ስጋት ተጋላጭነት ጥናት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡
ጥናቱ የተካሄደው በትምህርት ሚኒስቴር፣ በመንግሥትና በግል ዩኒቨርሲቲዎች፣ በፈተናዎች እና ምዘና አገልግሎት፣ በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ በተመረጡ የትምህርት ተቋማት ላይ ነው፡፡
ጥናቱ እንደሚያሳየው በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ብዛት ያላቸው የሙስና ስጋቶች ተለይተዋል፡፡
የመምህራን በተደጋጋሚ ክፍል አለመግባት፣ ሕገወጥ ቅጥር፣ ዝውውር እና ደረጃ ዕድገት፣ የአሠራር ግልጽነት መጓደል እና ግዥዎች ሕግና ደንብን ተከትለው አለመከናወን ጥናት ከተደረገባቸው ሁሉም ተቋማት ላይ ከተገኙ ክፍተቶች መካከል ይገኙበታል ተብሏል፡፡
ጥናቱ ለሙስና እና ብልሹ አሠራር ሊጋለጡ ይችላሉ የተባሉ የሥራ ክፍሎችን መለየቱም ተጠቁሟል፡፡
ግዥ፣ ፋይናንስ፣ የሰው ሃብት ልማት እና የንብረት ክፍሎች ለሙስና የመጋለጥ ከፍተኛ ዕድል እንዳላቸው ጥናቱ ማመላከቱን ኮሚሽኑ በላከልን መግለጫ አስታውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!