አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በቤት ልማቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ለቤት ልማት ብቻ የሚያገለግል ብሄራዊ የቤቶች ልማት ፈንድ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ መስፍን አሰፋ በቤት ልማቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የፋይናንስ ችግሩን በሚመለከት ለቤት ልማት ብቻ የሚያገለግል ብሄራዊ የቤቶች ልማት ፈንድ ለማቋቋም በርካታ ስራዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት።
በከተማ ቤት አቅርቦት ስትራቴጂ ላይ አማራጭ መንገዶችን ማስቀመጥ አለመቻል ትልቅ ክፍተት መሆኑን ያነሱት አቶ መስፍን፥ የህብረተሰቡን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አብራርተዋል።
በቤት ልማት ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።