አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2015 በጀት አመት ዕቅድ ትውውቅ እያካሄደ ነው።
ቢሮው “ከተሞችን የለውጥና የብልፅግና ማዕከል እናደርጋለን” በሚል መሪ ቃል ነው በደብረ ማርቆስ ከተማ የዕቅድ ትውውቁን እያካሄደ የሚገኘው፡፡
በመድረኩ እንደክልል የከተሞች የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት፣ የቤቶች መረጃ አስተዳደር ሂደት፣ ሕገ ወጥ ግንባታና የከተሞች አረንጓዴ ልማት ሥራ ይቀርባል ተብሏል፡፡
በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባራት ተገምግመው አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የአማራ ክልል የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ቢያዝን እንኳሆነ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ ባለፉት 10 ዓመታት በክልሉ የነበሩትን 261 ከተሞች አሁን ላይ 681 ማድረስ ተችሏል፡፡
ክልሉ በጦርነት ውስጥ ሆኖም ባከናወናቸው የልማት ተግባራት በቢሮው የ90 ቀናት ዕቅድ ከ81 ሺህ በላይ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ካለፉት አራት አመታት የበለጠ አፈፃፀም እንደሆነ ተናግረዋል።
“ስንቃችን ሥራችን ነው” ያሉት ኃላፊው ስንቅ የሌለው ረዢም ጉዞ መጓዝ አይችልምና አሁንም ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ባለፈው ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ተሞክሯቸውን ለውይይት አቅርበዋል።
በሙሉጌታ ደሴ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!