Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከናወኑ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከናወኑ አዋኪ ድርጊቶችን በመከላከል በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እንደተናገሩት÷ በትምህርት ዘመኑ ከመማር ማስተማሩ ባሻገር የትምህርት ቤቶችን አካባቢ ትኩረት ያደረጉ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡

በዚህም በትምህርት ቤቶች አካባቢ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውኩ፣ መጠጥ ቤቶችና መሰል ተቋማትን ተጽዕኖ የመከላከል ስራ በስፋት ይከናወናል ብለዋል።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የግብረ-ገብና የዜግነት ትምህርት እንዲሁም ለሥራና ክህሎት ስልጠና ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡

መልካም ስብዕና ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት የወላጆች፣ የትምህርት ተቋማት፣መምህራንና ሌሎችም አካላት ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ አዋኪ ድርጊቶችን በተደራጀ መልኩ መከላከል የሚያስችል ረቂቅ ህግ በአገር አቀፍ ደረጃ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ረቂቅ ሕጉ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version