Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሐረሪ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ህወሓት ለ3ኛ ዙር የከፈተውን ጦርነት አወገዙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ህወሓት ለ3ኛ ዙር የከፈተውን ጦርነት አውግዘዋል፡፡

በሐረሪ ክልል የሚኖሩ  የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ÷በአሸባሪው የህወሓት ቡድን  የተጀመረ ጦርነት ተቋጭቶ ሠላም ቢሠፍን ከሁሉም በላይ ትግራዋይ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች ተናግረዋል፡፡

መንግስት የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለመመከትና ለሠላም ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚደግፉ ነው ያስረዱት፡፡

አሸባሪው ህወሓት  ህፃናትን ለጦርነት ማሠማራቱን እና  የትግራይ ክልልን ትውልድ አልባ ለማድረግ የጀመረውን ጦርነት እንደሚያወግዙም አስታውቀዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ እና አሸባሪው  ህውሓት የተለያዩ በመሆናቸው  የሽብር ቡድኑ መንግስት የዘረጋለትን የሠላም እድል እንዲጠቀም  ፍላጎታቸው መሆኑንም አንስተዋል፡፡

መንግስት የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት እና የትግራይን ህዝብ ለመታደግ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም ኡመር በበኩላቸው÷ ጥቂት የሽብር ቡድኑ አባላት የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም በህዝብ ማዕበል የጀመሩት 3ኛ ዙር ጦርነትን ሊወገዝ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

አሸባሪው ህውሓት ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር ሀገር ለማፍረስ እያደረገ ያለውን እኩይ ዓላማ የትግራይ ተወላጆች በጽኑ ሊያወግዘት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

መንግስት የትግራይ ህዝብ  ደህንነት እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደሚያሳስበውም አስገንዝበዋል፡፡

 

በተሾመ ኃይሉ

Exit mobile version