አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁሉንም ክልል የምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች እና የከተማ አስተዳደር አፈ ጉባዔዎችን እና የተለያዩ የምክር ቤት አባላትን ያካተተ የአፈ ጉባዔዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ተሳታፊ ለሆኑት የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች እና የከተማ አስተዳደር አፈ ጉባዔዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አፈ ጉባዔዋ መድረኩ ኢትዮጵያዊያን ከጥንትም ይዘውት የቆዩትን የሕዝቦች የመፈቃቀር፣ የመመካከር እና የመደጋገፍ እሴት የበለጠ ለማጎልበት ያግዛል ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድ ዶክተር ይልቃል ከፋለ÷ ኢትዮጵያዊ ህብረ ብሔራዊነትን አጠናክሮ ለመቀጠል እና ሕዝቦችን የበለጠ ለማቀራረብ እንዲህ አይነት ምክክር ሁነኛ መንገድ ነው ብለዋል።
በየክልሉ ያሉ የመንግሥት ተወካዮች በተለይም የምክር ቤት አባላት በየክልሉ ያሉ ሕዝቦችን በማቀራረብና የጋራ እሴቶችን በማጠናከር በኩል በሰፊው መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የከፈተውን ወረራ ሙሉ በሙሉ ለመቀልበስና የበለጸገች ሀገር በትብብር ለመገንባት የቆየ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ሀገር ÷ አቀፍ የአፈ ጉባዔዎች መድረክ ዋና ዓላማ የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብና መፈቃቀርን ለማጠናከርና ሀገርን በጋራ ለመገንባት ያለመ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይለያዩ በአንድ የተገመዱ ናቸው ያሉት አፈ ጉባኤው ÷ የአሸባሪውን ሕወሓት ወረራ ለመቀልበስ በሚደረገው እንቅስቃሴም ሁሉም ኢትዮጵያዊውያን በጋራ ቆመው እየተፋለሙ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ምክር ቤቶች የሕዝብ ውክልና ያላቸው በመሆኑ ወጣቶችን፣ እናቶችን፣ የሀገር ሸማግሌዎችን እንዲሁም ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍሎች እርስ በርስ በማገናኘት ለአንድነታችን ሳንካ የሆኑ ጉዳዮችን በምክክር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።