የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የገበያ አሻጥርን እየተከላከለ መሆኑን ገለፀ

By Alemayehu Geremew

September 17, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የገበያ ማረጋጋትና የገበያ አሻጥርን እየተከላከለ መሆኑን ገለፀ።

አስተዳደሩ የኢኮኖሚ አሻጥርና ኑሮ ውድነት መከላከል ግብረ ሀይል የዘመን መለወጫ የገበያ አቅርቦትን ገምግሟል።

በዚህም በዘመን መለወጫ የገበያ አቅርቦት እና የገበያ ዋጋ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከክልል አምራቾች፣ ከማህበራትና ከባዛር ጋር በማስተሳሰር በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ መደረጉን ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል።

በስኳር እና በሲሚንቶ ላይ የገበያ አሻጥር የፈፀሙ ግለሰቦች ላይም ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው በግምገማው ተገልጿል።

ካለፈው በዓል ተሞክሮ በመውሰድ መጪው የመስቀል እና የኢሬቻ በዓል ላይ በዓሉ የሚፈልገውን አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ጃንጥራር አብራርተዋል።

ባለፈው የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የምርት አቅርቦት ላይ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም፥ በመጪው በዓላት የምርት ዋጋን ለመቀነስ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ ለፍጆታ ምርቶች መግዣ 1 ቢሊየን ብር መመደቡን የከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።