የሀገር ውስጥ ዜና

ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መድሃኒት ማምረት ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

By Amele Demsew

September 16, 2022

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለመድሃኒት አምራቾች ያለውን ምቹ እድል በመጠቀም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ፡፡

 

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አቅራቢዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

 

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንደገለጹት በአገልግሎቱ የግዥ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ 1 ሺህ 20 መድሃኒቶች ውስጥ በ970 ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 25 በመቶ ለሚሆነው መድኃኒት የተመዘገበ አቅራቢ የለውም፡፡

 

በተጨማሪም÷ 23 በመቶ የሚሆነው የመድኃኒት አቅርቦት በአንድ አቅራቢ መያዙን እና 49 በመቶ የሚሆኑት አንድና ከዛ በታች የተመዘገበ አቅራቢ ያላቸው መሆኑን የዳሰሳ ጥናቱ እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡

 

የአቅራቢዎችን ውስንነት ለመፍታት መድሃኒትና የህክምና ግብአቶችን ማስመጣት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች መንግስት የሚሰጠውን ማበረታቻ በመጠቀም ዘርፉን እንዲቀላቀሉም ሀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

 

በዘርፉ ለሚሰማሩ አምራችና አቅራቢዎች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑም ተገልጿል፡፡

 

በመድሃኒትና ህክምና መገልገያ አስመጭነት የተሰማሩ ባለሃብቶች በበኩላቸው÷ በዘርፉ በአምራችነት ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

 

ጉባኤውው በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚገኙ የገበያ አማራጮች ላይ መረጃዎችን በማስተዋወቅ የመድሃኒት አምራችና አቅራቢዎችን መሳብ ታሳቢ ያደረገ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡