የሀገር ውስጥ ዜና

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ ተሻሻለ

By ዮሐንስ ደርበው

September 16, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ መሻሻሉን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የግል መገልገያ እቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ የሚወስነው በሥራ ላይ ያለው መመሪያ ለሕገ ወጥ ንግድ በር የከፈተና የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተፅዕኖ የፈጠረ በመሆኑ በመመሪያ ቁጥር 923/14 መተካቱን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡

ቀድሞ በነበረው መመሪያ ከቀረጥና ታክስ ነፃ ሆነው በመንገደኞች እንዲገቡ የተፈቀዱ 102 ዓይነት እቃዎች ወደ 16 ዓይነት ወይም 84 በመቶ ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል።

ከውጭ አገር ተመላሽ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ለ12 ወራት ሲገለገሉባቸው የነበሩትን የግል መገልገያ እቃዎች ከቀረጥ ታክስ ነፃ ማስገባት እንደሚችሉም ተመላክቷል፡፡

የግል መገልገያ እቃ በስጦታ የተላከለት ሰው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የሌለው ከሆነ ከቀረጥና ታክስ በተጨማሪ 30 በመቶ የገቢ ግብር ይከፍላል መባሉን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ ከሁለት ጊዜ በላይ ስጦታ መቀበል እንደማይቻልም ተገልጿል፡፡