Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ መረጃዎችን በመጠቀም ረገድ የሃይማኖት ተቋማትን አቅም ማጎልበቻ መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ መረጃዎችን እና የተግባቦት መንገዶችን በመጠቀም ረገድ የሃይማኖት ተቋማትን አቅም ማጎልበቻ መርሐግብር ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በጋራ የተዘጋጀ የኮቪድ 19 መከላከያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ይፋ ተደርጓል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ÷ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል በማቋቋም የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ በመሆኑ ወረርሽኙ የሚያስከትለውን የከፋ ጉዳት መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

በማህበረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን በመሙላት የማህበረሰብ ንቅናቄ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የኮቪድ 19 ወረርሽኝን የመከላከል ስራዎችን በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

የተሳሳቱ መረጃዎችን እና አመለካከቶችን ለማረምና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይረዳ ዘንድ የኮቪድ-19 መከላከያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ከሃይማኖታዊ እና ከሳይንሳዊ እይታ አንጻር ተዳሶ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ሊቀ ትጉሓን ታጋይ ታደስ (ቀሲስ) ÷በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ መረጃዎች የቫይረሱን ስርጭት እና የሚያደርሰውን የጤና ጉዳት ለመቀነስ ታስቦ የሚሰራውን የመከላከል ስራ ፈታኝ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

ክትባቱን እና ሌሎች ጤናን አስመልክቶ የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎች በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ተቀባይነት እንደሌላቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ረገድ የሃማኖት አባቶችም ለማህበረሰቡ አርአያ መሆን እና ማስገንዘብ እንዳለባቸው መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version