የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ሌንጮ የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ

By Meseret Awoke

September 15, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲያውሉ ጥሪ አቀረቡ።

አምባሳደር ሌንጮ ከቪአይኤ መርከብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ምክትል ሊቀመንበር ቱርኪ አልማዲ እና ከባልደረቦቻቸው ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትን የትኩረት አቅጣጫዎች ያብራሩት አምባሳደሩ ፥ የሳዑዲ ባለሀብቶች በዘመናዊ ግብርና፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ዘርፎች ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ነው የጠየቁት።

ባለሀብቶቹም ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲመለከቱ መጋበዛቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የሳዑዲ የቪአይኤ መርከብ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የስራ ባልደረቦቻቸው በበኩላቸው ፥ ኩባንያው በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ኢነርጂ፣ ባንክና ቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

አክለውም፥ በቅርቡ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንቨስትመንት ላይ ለመሳተፍ እያሰቡ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!