Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአሸባሪው ህወሓት ተማፅኖ ጊዜ ለመግዛት ነው – ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጄራልድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን የሚሰማው የአሸባሪው ህወሓት የተኩስ አቁም ተማፅኖ ለዘላቂ ሠላም ዕድል ለመስጠት ሳይሆን ከደረሰበት ኪሳራ ለማገገም መሆኑን ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጀራልድ ገለጹ፡፡

እንደ አን ፊትዝ-ጀራልድ ገለጻ አማፂው ኃይል አሁን ላይ ኅጋዊ ሂደቱን ያላሟላ የተኩስ አቁም ተማፅኖ የሚያቀርበው እና ስለ ሠላም መግለጫ የሚያወጣው የቀረ ኃይሉን አሰባስቦ ለቀጣይ ጦርነት ለመዘጋጀት ነው፡፡

ፕሮፌሰር አን ፊትዝጌራልድ በካናዳ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉዳዮች ተመራማሪ እና የባልሲሊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዲን ናቸው፡፡

በሚያሰራጨው ማደናገሪያ እፎይታ ካገኘ አሁንም የጦር መሣሪያ ግዢ መፈጸሙን እና የጦር ኃይሉን አጠናክሮ አጎራባች ክልሎችን መውረሩን እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግስት በአጎራባች አካባቢዎች ያሉ ዜጎቹን ሠላም እና ደኅንነት እንዲሁም ድንበሩን የማስከበር እና ሉዓላዊነቱን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበትም ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ አማፂ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ወይም በሽብር ተግባር መሠማራቱን የሚቀጥል ከሆነ መንግስት ቁጭ ብሎ ማየት እንደሌለበትና የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።

በዓለም አቀፉ ኅግ መሠረት በማናቸውም ሁኔታዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለተጎዱ አካባቢዎች መድረስ እንዳለበትና ይህን ለማድረግም የሚያስችል ከጦር ቀጣና ነጻ የሆነ መተላለፊያ (ኮሪደር) እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰሯ አንስተዋል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን አካባቢ በተለይም የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልገውን የኅብረተሰብ ክፍል አስተዳደራዊ መዋቅር የተቆጣጠረው ደግሞ አማፂ ቡድኑ በመሆኑ ዕርዳታው በትክክል ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ለማቅረብ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ አጋርተዋል፡፡

በጦር ቀጣና ተፈጻሚ እንዲሆን የተቀመጠውን ዓለም አቀፉን የሰብዓዊነት ኅግ ቡድኑ እንደተለመደው እንደሚጥሰውና ድጋፉንም ለሽብር ተግባር ለመለመላቸው ታጣቂ ኃይሉ እንደሚያደርገውም ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል ጦርነቱ በማንኛውም መስፈርት አክሳሪ እና መቀጠል የሌለበት እንደሆነ ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም አውጆ እንደነበር አስታውሰው ለሶስተኛ ዙር የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲቆም ከመንግስት ወገን ብቻ ሳይሆን አማጺው ቡድንም ለሠላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ይፋዊ የተኩስ አቁም መግለጫ ማውጣት አለበት ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ይረዳው ዘንድ ጦርነቱ በሉዓላዊ ሀገረ መንግስት እና በምርጫ ተሸንፎ ባኮረፈ አማጺ ቡድን መካከል የሚካሄድ መሆኑን ማስታወስ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።፡

በወንደሰን አረጋኸኝ እና ዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version