የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ህብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

By Tibebu Kebede

March 18, 2020

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተከታታይ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ እንዲያስችል እቅድ በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ ከሰሞኑ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ አስቀድሞ ለመከላከል እና ህብረተሰቡ ስለቫይረሱ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባ ፅህፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነስረዲን ማሕሙድ እንደገለጹት፥ ህብረተሰቡ ስለቫይረሱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል እና ከቫይረሱ ጋር ተያያዥ የሆኑ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እስከ ወረዳ ድረስ የኮሙዩኒኬሽን መዋቅር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን በማሳተፍ እየተሰራ ነው።

በትራንስፖርት እና ህዝብ የሚበዛባቸው ቦታዎች ለህብረተሰቡ የቅድመ ጥንቃቄ መረጃዎችን ከማድረስ በተጨማሪ የንጽህና መጠበቂያ እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ መናገራቸውን ከከተማዋ ፕሬስ ሴክሪታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እና የተሳሳተ መረጃዎችን የሚሰጡ አካላትን በማጋለጥ ያሳዩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።