Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አዲስ የሲሚንቶ ዋጋ ተመን ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እየጨመረ የመጣውን የሲሚንቶ ምርት ዋጋ ለማስተካከል አዲስ የዋጋ ተመን ማውጣቱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ እየናረ የመጣውን የሲሚንቶ ምርት ዋጋ ለማስተካከል ፋብሪካዎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተጠይቀው ያወጡት ዋጋ እጅግ የተጋነነ በመሆኑ ነው በዘርፉ ያለውን የምርት ሂደት ጥናት የሚያደርግ ቡድን በማቋቋም አዲስ የዋጋ ተመን ይፋ ያደረገው፡፡

በዚህ መሰረት ሲሚንቶ ከፋብሪካ የሚወጣበት አዲሱ የዋጋ ተመን ዝቅተኛው 510 ብር ሲሆን÷ ከፍተኛው ደግሞ 683 ብር ከ44 ሳንቲም እንዲሆን ተወስኗል፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ÷ አሁን ላይ የሲሚንቶ ምርት እጥረት በመኖሩ ለመንግስታዊ ስራዎች ቅድሚያ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችም ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም ማረጋገጫ በማምጣት ከፋብሪካዎች በቀጥታ ምርት የሚገዙበት መንገድ ተመቻችቷል ነው ያሉት፡፡

የግል ተጠቃሚዎችን በተመለከተም የሁሉም ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ፍላጎት ምን ያህል እንደሆነ ስለሚታወቅ በመንግስት የልማት ድርጅቶችና በተደራጁ ማህበራት በኩል እንደሚያገኙ አስረድተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ይሁንታ ካገኙ አካላት ውጪ ሲሚንቶ ይዞ የሚገኝና በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ግብይቶች ህገወጥ በመሆናቸው ተቋሙ ማስታወቂያ ካስነገረበት ቀን ጀምሮ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version