Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በህንድና በኢትዮጵያ መካከል ያለው መልካም ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ትስስርና ድጋፍ አበረታች በመሆኑ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ደረጃ ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በኢትዮጵያ ከህንድ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ÷ ኢትዮጵያና ህንድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት መስክ እና በሌሎች ዘርፍ ብዙ የልማት ስራዎች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍም የህንድ ባለሃብቶች በዘርፉ መዋዕለንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ ፣ ከሌሎች ሀገራት አኳያም የተሻለ ትብብር እንዳላቸውና ኢትዮጵያም ተጠቃሚ መሆኑዋን በማውሳት አመስግነዋል፡፡

ህንድ ለኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ከሌሎች ሴክቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በምታደደርገው ዘርፈ-ብዙ ትብብርና የድጋፍ ስራዎችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ተናግረዋል፡፡

ቀደም ብለው የተጀመሩትንና በኮቪድ -19 ወረርሽኝ የተቀዛቀዙ የትብብር ማዕቀፎችንም በማደስ ወደ ስራ ለማስገባት በጋራ ለመስራት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግን በበኩላቸው ህንድ ሁል ጊዜ የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነት እና ሉዓላዊነት የምታከበር ሀገር መሆኑን ገልጸው፥ በንግድና ኢንቨስትመንት ከ500 በላይ ወደ ስራ የገቡ የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለው ስራ ትስስርና ድጋፍ አበረታች ስለሆነ በቀጣይም ከዚህ በተሻለ በጋራና በትብብር መሰራት እንዳለበት መናገራቸውን ከኢኖቬሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version