አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግርግርና ሁካታ ከተጨናነቀው ከተማ ይልቅ በተፈጥሮ ልምላሜ የታደለው ገጠራማ አካባቢ መንፈስን ለማደስ የተሻለው ስፍራ መሆኑ ይታመናል።
ጥናቶች ደግሞ በተፈጥሮ በታደሉ አካባቢዎች ረዘም ላለ ጊዜ የእግር ጉዞ ማድረግ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው ያመላክታሉ።
ጥናቱ ከአዕምሮ ጤና እና ጭንቀት ጋር በተያያዘ በገጠር እና በከተሞች አካባቢ ጥናቶች ተደርገዋል።
በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በገጠር ከሚኖሩት በበለጠ ለአዕምሮ ህመም የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ነው የጥናቱ ውጤቶች የሚያመላክቱት።
ከዚህ ጥናት በመነሳት በጀርመን ማክስ ፕላንክ የነርቭ ሳይንስ ተመራማሪዎች ባደረጉት የቅርብ ጊዜ ጥናት ተፈጥሮ ከአዕምሮ ጤና ጋር ተዛምዶ እንዳለው ገልጸዋል።
ጥናቱ እድሜያቸው ከ18 እስከ 47 በሚደርሱ 34 ወንዶች እና 29 ሴቶች የተደረገ ሲሆን፥ የጥናቱ ተሳታፊዎች ከአዕምሮ ጤና ጋር የተያያዙ ምርመራዎችና የሂሳብ ቀመሮችን እንዲፈቱ ተደርጓል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች በተጨናነቁ የከተማ ጎዳናዎች እና ፀጥ ባሉና በተፈጥሮ ልምላሜ በታደሉ አካባቢዎች ለአንድ ሰአት የእግር ጉዞ አድርገዋል።
በዚህም 31 ተሳታፊዎች በበርሊን የተጨናነቁ ጎዳናዎች ላይ የእግር ጉዞ ሲያደርጉ፥ 32ቱ ደግሞ ተፈጥሮ በታደሉ አካባቢዎች ነው የእግር ጉዞ ያደረጉት።
በጉዟቸው ወቅትም ያሉበትን ስፍራ መከታተያ፣ የልብ ምታቸውን እና አጠቃላይ ሁኔታዎችን የሚከታተልና የሚቆጣጠሩ መሳሪያዎች ተገጥመውላቸዋል።
ተሳታፊዎች ጉዟቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ልምላሜ በታደሉ ተፈጥሯዊ ቦታዎች የእግር ጉዞ ያደረጉት ተሳታፊዎች ላይ ይስተዋል የነበረው የጭንቀትና ፍርሃት በእጅጉ መቀነሱን ጥናቱን በዋናነት የመሩትና የስነ አዕምሮ እና ስነ ልቦና ህክምና ባለሙያ የሆኑት ሶኒያ ሱዲማክ ገልጸዋል።
ይህም የሚያመላክተው በተፈጥሮ በታደሉ ስፍራዎች ውስጥ ለሰዓታት የእግር ጉዙ ማድረግ የአዕምሮ ጭንቀትን ለመቀነስ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ስለ ሁኔታው ሲያብራሩም ለጭንቀት መንስኤ የሆነው የኮርቲሶል ሆርሞን ከ15 ደቂቃዎች የእግር ጉዞ በኋላ በእጅጉ እንደሚቀንስና ጠቅሰዋል።
ለዚህ ደግሞ ከከተማው ግርግር ይልቅ የተፈጥሮ ልምላሜ በታደሉ ስፍራዎች ያለው ነባራዊ ሁኔታ አዕምሮን ዘና የማድረግ አቅም እንዳለውም ያስረዳሉ።
ከዚህ በታቃራኒው ግን ግርግር ባለባቸው የከተሞ ጎዳናዎች የእግር ጉዞ ያደረጉት ታሳታፊዎች ይታይባቸው የነበረው ጭጥንቀት አለመቀነሱን እና ያለመረጋጋት ስሜት ይታይባቸው እንደነበር ነው የጥናት ውጤቱ ያመላከተው።
አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች ግኝቱን በተለያየ መልኩ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናቶች መደረግ አለባቸው ማለታቸውን ሜዲካል ኒውስ ቱደይ ዘግቧል።