የሀገር ውስጥ ዜና

አትዮጵያ አዲስ ዓመቷን ተቀበለች

By Mekoya Hailemariam

September 11, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት 2015 ዛሬ ገብቷል።

ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሁነቶች አዲስ ዓመታቸውን ተቀብለዋል።

በዓሉን በማስመልከትም በማለዳው 12 ሰዓት ላይ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

አዲስ ዓመትን በማስመልከት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት መልዕክት፥ 2014 ዓመተ ምህረት በብዙ መልካምና እኩይ አጋጣሚዎች ተሞልቶ ማለፉን አስታውሰዋል።

“አዲሱን ዘመንን በጉጉት ስንቀበለው እንደ መስከረም አደይ ተስፋችን እንደሚፈካ፣ እንደ አዝመራው ውጥናችን ፍሬ አፍርቶ እንደምናይ፣ እንደ በጋ ወንዝ ሰላማችን ከአደፍራሾች እንደሚጠራ፣ ጭጋግ ጭለማው ከላያችን ተገፍፎ ብርሃን እንደሚፈነጥቅብን በመተማመን ነው” ብለዋል በመልካም ምኞት መልዕክታቸው።

“አሁን አንድ፣ ምንም ያልተነካ ተአምር ሊሠራበት የሚችል ውድ ሀብት ከፊታችን ቆሞ ይጠብቀናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

“አዲስ ዓመት ማክበር ትርጉም የሚኖረው በጊዜ ውስጥ ለማለፍ የምንችል ከሆነ ነው። ጊዜ ይዞን ለሚሄድ ሰዎች አዲስ ዓመት የሚባል ነገር የለም” ብለዋል።

“አዲሱን ዓመት አዲስ እናድርገው። በራሱ ጊዜ የሚሄድና የሚመጣን ዓመት፣ አዲስና አሮጌ ማለት ትርጉም የለውም። የራሳችንን አዲስና አሮጌ ዘመን እንፍጠር።” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

“ዘመኑን በአዲስ ሥራ አዲስ አድርገነው አዲስ ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ” በማለትም መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።