የሀገር ውስጥ ዜና

የአንድነት ቀን በፕሪቶሪያና ፓሪስ የኢፌዴሪ ኤምባሲዎች ተከበረ

By Mekoya Hailemariam

September 10, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንድነት ቀን በፕሪቶሪያ እና ፓሪስ የኢፌዴሪ ኤምባሲዎች ተከበረ።

ቀኑ በፕሪቶሪያ የኢፌዴሪ ኤምባሲ አዘጋጅነት “አንድነታችን በዘመናት አብሮነታችን የተገነባ እሴታችን ነው” በሚል መሪ ቃል በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ የሀይማኖት መሪዎች፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አመራሮች፣ ምሁራን፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በድምቀት ተከበሯል።

በስነ ስርዓቱ ላይ፥ በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር፥ አንድነት ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ እና ለሀገር ቁልፍ ተፈላጊ እሴት መሆኑን ተናግረዋል።

የህዝብ አንድነቱ ያልጎለበተ ሀገር ደካማ መሆኑ አይቀርም ያሉት አምባሳደር ሙክታር፥ የውጭ ጠላቶቻችንን ለመመከት ብቻ ሳይሆን የውስጥ ችግሮቻችንን ለመፍታት አንድነታችን ያስፈልጋል ብለዋል።

በተመሳሳይ ዕለቱ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በፓሪስ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ተከብሯል::

በእለቱም የሚሲዮኑ መሪ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ ባስተላለፋት መልእክት፥ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ነፃነቷን እና የግዛት አንድነቷን አስከብራ የዘለቀችው ዜጎቿ በነበራቸው አንድነት የውጭ ወራሪ ሃይሎችን በመመከትና ድል በማድረግ እንደሆነ አስታውሰዋል።

የአሁኑ ትውልድም አገራችን በገጠማት ጊዚያዊ ችግሮች ሳይበገር የአገሩን ሉዓላዊ አንድነት በማስጨበቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቷን እንዲያፋጥን አሳስበዋል።

በእለቱ ተሰብሳቢዎች ለአገራቸው አንድነት እና ብልጽግና የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁነታቸውን እንዳረጋገጡ ከኤምባሲዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።