አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ ለ2015 አዲስ ዓመትን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፥ 2014 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይደረግ ዓለም አቀፍ ጫና የበረታበት እና አሸባሪው ህወሓት ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ጋር አብሮ ሀገራችን ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደሩበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ጫናዎችን በጋራ አክሽፈው በአሸናፊነት ያለፉበት ዓመት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
አዲሱን ዓመት ስንቀበል ካለፈው ዓመት በጎነትን፣ መረዳዳትንና መደጋገፍን በማስቀጠል እንዲሁም ለላቀ ብልፅግናና ከፍታ በመትጋት መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አቅመ ደካሞችን በመርዳት እና ማዕድ በማጋራት እንዲሆን መጠየቃቸውን ከክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሀገርና ሕዝብን ከጉዳት ለመከላከል ህይወት እየከፈሉ ላሉ ጀግኖች ደጀን በመሆን፣ ክብርና ፍቅር በመስጠት ብሎም በአሸባሪዎች ጭካኔ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ አዲሱን ዓመት ልናከብር ይገባልም ነው ያሉት።
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የድል፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።