በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የሚገባትን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይገባል – አቶ አወል አርባ  

By Shambel Mihret

September 10, 2022

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የሚገባትን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይኖርብናል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ፡፡

አቶ አወል አርባ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን÷አዲሱ አመት የሰላም የብልፅግና፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ዓመት የጀመርናቸው የልማት፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ጉዟችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ የምናሸጋግርበት፣ ከጦርነትና ከጥላቻ ይልቅ ለሰላም እና ለፍቅር የምንሰራበት፣ ድህነት እና ኋላ ቀርነትን በማስቀረት ወደ እድገት መስመር የምንገባባት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡

ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ልዩነቶችን ባከበረ መልኩ ሉዓላዊነት አስከብረን ወደ ቀጣዩ አመት የምንሸጋገርበት እንዲሆን ከምኞት ባለፈ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የራሱን ጡብ የሚያስቀምጥበት ግንባታ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያን ክብር እና ሰላም ማስጠበቅ የሁላችንም ሀላፊነት መሆኑን በመገንዘብ ለሀገሬ ምን ሰራሁ፣ በአዲሱ ዓመትም ምን መስራት አለብኝ በማለት ራሳችንን በመጠየቅ ለሀገሪቱ የሚገባትን አገልገሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይኖርብናል ብለዋል።

አያት ቅድመ አያቶቻችን ሀገራችን ከእነሙሉ ክብሯ ጠብቀው ለኛ ያስረከቡት መስዋዕትነት በመክፈል፣ ስግብግብ ራስ ወዳድነትን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ክብር በህብረትና በጋራ በመቆም ለነገው ትውልድ በማሰብ ታሪክ ሰርተው በማለፋቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአሁኑ ትውልድ “ታሪካችን በጎውም መጥፎውም የኛ መሆኑን በመገንዘብ በጎውን በማስቀጠል፣ ከመጥፎው ደግሞ ትምህርት በመውሰድ መሰል ጥፋቶች እንዳይደገሙ እና የተሻለ ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ ጥረት ማድረግ“ እንደሚኖርበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በ2014 አመት ምህረት በሀገር ውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ሀይሎች የእጅ አዙር ጦርነት እና ተያያዥ ተግዳሮቶች በርካታ ችግሮችን ተጋፍጠናል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በከፈተው ጦርነት በከባድ መሳሪያ ንፁሀን ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶቸን ያለምንም ርህራሄ ጨፍጭፏል፣ በርካቶቸን ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል ለሞት፣ ለከባድ ስቃይና እንግልት ዳርጓል ነወቅ ያሉት።

እንደ አፋር በአራት ዞኖች ወረራ በማካሄድ ከባድ የሆነ ኪሳራን አድርሷል፣ የአፋር ህዝብ ታሪካዊ ጠላት መሆኑን በይፋ አስመስክሯል ብለዋል በመልዕክታቸው።

የክልሉ ህዝብም ከልዩ ሀይሉ፣ ሚሊሻውና ህዝባዊ ሰራዊቱ ጋር የአሸባሪው ህወሓትን ወረራ ለመመከት ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድ ድምፅ በመነሳት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ታላቅ ጀብድን መፈጸሙን አንስተዋል፡፡

በአፋር በኩል በመግባት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለመበታተን የነበረውን የአሸባሪው ህወሓት ከንቱ ምኞት መና ማስቀረት ተችሏል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

የተከፈተውን ጦርነት እየመከትን ልማታችንንም ማስቀጠል ስለሚገባን በአምራች ዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም ሊመዘገብ መቻሉንም አውስተዋል።