የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ

By Mekoya Hailemariam

September 10, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ።

 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመልካም ምኞት መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

 

እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

 

ዘመን አልፎ ዘመን ሊተካ፣ አሮጌ ምዕራፍ ተዘግቶ አዲስ ምዕራፍ ሊገለጥ፣ መጪውን ዘመን ልንቀበለው በምንዘጋጅበት በዛሬው የዋዜማ ምሽት ላይ ሆነን፣ ዐይነ ሕሊናችን ያሳለፍነውን ዓመት በትውስታ፣ መጭውን ደሞ በአዲስ ተስፋ ማስተናገዱ አይቀርም።

 

ያገባደድነውን ዓመት ስናስብ ትውስታችን በብዙ መልካምና እኩይ አጋጣሚዎች ተሞልቶ እናገኘዋለን። በአንድ በኩል ዓመቱ ጠላቶቻችን ግንባር ፈጥረው ጥቃታቸውን ያጠነከሩብን፣ ገሚሶቹ በሀገር ውስጥ ንጹሐን ለሞት ጭዳ ሊያደርጉ ጦር ያዘመቱበት፣ ገሚሶቹ በውጪ ዓለም አቀፍ ጫና በሚያሳድሩ መድረኮችና ሚዲያዎች አማካኝነት የቅጥፈት ዘመቻ ያጧጧፉበት፣ እንደ ሀገር የተፈተንንበት ዓመት ነው።

 

በሌላ በኩል ተስፋችንን የሚያለመልሙ፣ ወደፊት እንድንጓዝ ስንቅ የሚሆኑ ድሎች የተመዘገቡበትም ዓመት ነበር። ተደራጅተው በዘመቱብን ቁጥር ተደራጅተን መመከት እንደምንችል ያሳየንበት፣ የማዕቀብ ውርጅብኞችን መሻገር ወደሚያስችሉ መንገዶች ጥርሳችንን ነክሰን የገባንበት፣ በምግብ ራስን የመቻል ጉዟችን ተስፋ የፈነጠቀበት፣ ሉአላዊነታችን እንዲታፈር የሚያስችል ዐቅም እንድናደረጅ እድል የተፈጠረበት ጊዜ ስለነበር፣ ዓመቱን በምሬት ብቻ ሳይሆን በምስጋናም ጭምር እንድናስበው ያደርገናል።

 

አዲሱን ዘመንን በጉጉት ስንቀበለው እንደ መስከረም አደይ ተስፋችን እንደሚፈካ፣ እንደ አዝመራው ውጥናችን ፍሬ አፍርቶ እንደምናይ፣ እንደ በጋ ወንዝ ሰላማችን ከአደፍራሾች እንደሚጠራ፣ ጭጋግ ጭለማው ከላያችን ተገፍፎ ብርሃን እንደሚፈነጥቅብን በመተማመን ነው። ይኽ እምነታችን እንዲሳካ ከዘመኑ ጋር እኛም አብረን መቀየር ይኖርብናል። ምክንያቱም የእኛ መለወጥ ነው የዘመኑን ለውጥ እውነተኛ የሚያደርገው። እኛ ሳንቀየር፣ አሮጌ አስተሳሰባችንን አውልቀን ሳንጥል፣ ዓመት ሄዶ ሌላ ዓመት ቢመጣ የዘመን ለውጡ የቁጥር እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።

 

ውድ የሀገሬ ልጆች፣

 

አሁን አንድ፣ ምንም ያልተነካ ተአምር ሊሠራበት የሚችል ውድ ሀብት ከፊታችን ቆሞ ይጠብቀናል። የመለወጥ እድሎችን የያዘ ዓመት። ዓመቱ ብንጠቀምበትም ባንጠቀምበትም መሄዱን አይተውም። ልክ እንደ ወራጅ ውኃ ያገኘውን ሁሉ ይዞ ይጓዛል። ከልደት እስከ እርጅና፣ ከእርጅናም እስከ ሞት ያደርሳል። መምሸትና መንጋት፣ ሳምንታትና ወራት፣ ዓመታትና ዘመናት ከኛ ቁጥጥር ውጭ ናቸው። ወቅቶችና ጊዜያትን መቁጠር ብቻ፣ መኖርን የማይገልጠው ለዚህ ነው። ውኃ ይዞት የሄደ ሁሉ ዋናተኛ አይባልምና። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ከዋናተኛ በላይ ውኃ ይዞት የሚሄድ ነገር በፍጥነት ይጓዛል። ችግሩ፣ ፍጥነቱ ወዳልፈለገው ቦታ ይዞት እየተላተመ በመከራ ይጓዛል።

 

በጊዜ ውስጥ መሄድ ግን ከዚህ ሁሉ ይለያል። በማይቀየረው ጊዜ የሚቀየር ታሪክ ለመሥራት መጓዝ ነው። ሲቻል ከጊዜ መቅደም፣ ሳይቻል ከጊዜ ጋር አብሮ መጓዝ ነው። በጊዜ ውስጥ መጓዝ ጊዜ ወደሚወስደው የተለመደ ጉዞ ሳይሆን በጊዜ ውስጥ ልናሳካው ወደምንፈልገው ግብ ለመጓዝ መቻል ነው።

 

አዲስ ዓመት ማክበር ትርጉም የሚኖረው በጊዜ ውስጥ ለማለፍ የምንችል ከሆነ ነው። ጊዜ ይዞን ለሚሄድ ሰዎች አዲስ ዓመት የሚባል ነገር የለም። የጊዜ ዑደት ከጥንት እስከዛሬ የታወቀ፣ የተለመደ ነገር በመሆኑ። በሌሎች ያልተደረገ ነገር በእኛ ላይ ስለማይደረግ፤ ከዚህ በፊት ያልሆነ ነገር ዛሬ አዲስ ነገር ስለማይሆን። ሁሉም ቀናት፣ ሁሉም ሳምንታት፣ ሁሉም ወራት አምናም ነበሩ።

 

በጊዜ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች አዲስ ዐሻራ በየዘመኑ ያሳርፋሉ። ትናንት ያልታሰበና ያልተደረገ አዲስ ዐሻራ። ታሪክን ይቀይሩታል፤ አስተሳሰብን ይቀይሩታል፤ የሰውን ልጅ የአኗኗር ዘይቤ ይቀይሩታል። አዲስ ዕይታ፣ አዲስ ዓለም፣ አዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ መንገድ፣ አዲስ ሀብት፣ አዲስ ቴክኖሎጂ፣ አዲስ፣ አሠራር፣ አዲስ ዘይቤ ይፈጥራሉ። በዚህም ምክንያት ትናንትን ከትናንት ወዲያ፣ ዛሬን ከትናንት፣ ነገን ከዛሬ ይለዩታል። አዲስ ነገር በማድረግ፣ ዘመኑ ብቻ ሳይሆን ቀኑም አዲስ እንዲሆን ያደርጋሉ። ዓለም ዘወትር ስታስታውሳቸው የምትኖረው እንዲህ ያሉትን ሕያው ሰዎች ነው። ጊዜ ብዙዎችን ሲሽር በማይሻር ሥራቸው ሕያውነትን ተጎናጽፈው ጊዜን ራሱን አሸንፈውታልና።

 

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

 

ሀገራችን ጊዜን የሚያሸንፉ ሕያዋን ዜጎች ትፈልጋለች። ዘመኑ እንደ ቁጥሩ አዲስ እንዲሆንላት አዲስ ሥራ በአዲሱ ዘመን የሚሠሩ ዜጎች ትፈልጋለች። ነባር ችግሮቿን በአዳዲስ መፍትሔዎች የሚተኩ፤ ነባር ፈተናዎቿን በአዳዲስ መድኃኒቶች የሚፈውሱ፤ ነባር ዕንቅፋቶቿን አንሥተው አዳዲስ መንገዶች የሚገነቡ፤ የተለመዱ የታሪክ አንጓዎቿን በአዳዲስ የታሪክ ምዕራፎች የሚቀይሩ፤ የርሃብ ታሪኳን በብልጽግና፤ የጦርነት ታሪኳን በዘላቂ ሰላም፤ የመከፋፈል ታሪኳን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት፤ የግጭት ታሪኳን በወንድምና እኅታማችነት፤ የኋላቀርነት ታሪኳን በዘመናዊነት፤ የሚቀይሩ ሕያዋን ጀግኖች ትፈልጋለች። አዲሱ ዓመት በርግጥም አዲስ እንዲሆንላት አዲስ ታሪክ የሚጽፉላትን ትፈልጋለች።

 

የዘንድሮ መስከረምና ጥቅምት፣ የካቲትና ግንቦት ካምናው፣ ከካቻምናው፣ ከጥንቱ፣ ከቀደምቱ የተለየ ሆኖ እንዲከበር የሚያደርጉ፣ ዘመን ቀያሪ ልጆች ትፈልጋለች። የዘመን መቀየር አይቀሬ ነገር ነው። ዘመንን ራሱን መቀየር ግን የጀግኖች ሥራ ነው። አረንጓዴ ዐሻራ፣ የበጋ ስንዴ፣ የቱሪዝም ሀብቶቻችንን በራሳችን ዐቅም የመጠቀም ጅማሮ፣ ሀገራዊ ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት ውጥን፣ ከውጭ ተጽዕኖ ለመላቀቅ በገቢ ራስን የመቻል እንቅስቃሴ፣ የዚሁ አካል ነበሩ። ዘመንን የመቀየር ፍላጎት ውጤቶች።

 

እነዚህ ግን ማሳያዎች እንጂ ፍጻሜዎች አይደሉም። አገልግሎት አሰጣጥን ከሌቦች በማጽዳት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ በማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን ጫና በመቀነስ፣ የአምራች ዘርፉን ድርሻ በማሳደግ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር፣ ግጭቶችን በማስወገድ፣ ግብርናን ይበልጥ በማዘመን፣ የውጭ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠናከር፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ዴሞክራሲን በማጽናት፣ ያለንን የተፈጠር ጸጋ በሚገባ በመጠቅም፣ ወዘተ. የሚቀሩን ነገሮች አሉ። እነዚህ ሁሉ፣ ዘመን የሚቀይሩ ጀግኖችን ይፈልጋሉ።

 

አዲሱን ዓመት አዲስ እናድርገው። በራሱ ጊዜ የሚሄድና የሚመጣን ዓመት፣ አዲስና አሮጌ ማለት ትርጉም የለውም። የራሳችንን አዲስና አሮጌ ዘመን እንፍጠር። አሮጌው ዘመን ለዕጽዋትም፣ ለእንስሳትም፣ ለግዑዝ ነገሮችም አሮጌ ሆኗል። አዲሱ ዓመትም ለእነዚህ ሁሉ አዲስ ነው። ሰው የመሆናችን ልዩነት የሚፈጠረው የራሳችንን አዲስ ዓመት ራሳችን ስንፈጥረው ነው። ያን ማድረግ የምንችለው ደግሞ አዲስ ሥራ በመሥራት ነው። አምና ያልነበረ ለውጥ፣ ሥራና ተአምር ከፈጠርን ዓመቱ አዲስ ዓመት ይሆናል፤ በአምናው በሬ ዘንድሮም ካረስን ግን ምኑን አዲስ ዓመት ሆነው ለኢትዮጵያችን አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮች፣ አዳዲስ መፍትሔዎች፣ አዳዲስ መንገዶች፣ አዳዲስ ዕይታዎች፣ አዳዲስ ዐሻራዎች፣ አዳዲስ ምርቶች፣ አዳዲስ የኪነ ጥበብ ሥራዎች፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች፣ አዳዲስ ፍልስፍናዎች፣ አዳዲስ የአገልግሎት አሰጣጥ መንገዶች፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች፣ አዳዲስ መሠረተ ልማቶች፣ አዳዲስ የዕውቀት ብልጭታዎች፣ አዳዲስ የግብርና ዘይቤዎች በማምጣት ዘመኑን አዲስ እንድናደርገው ጥሪዬን አቀርባለሁ።

 

በድጋሚ ዘመኑን በአዲስ ሥራ አዲስ አድርገነው አዲስ ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ።

 

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

 

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጳጉሜን 5፣ 2014 ዓ.ም