ቢዝነስ

በአማራና ሲዳማ ክልሎች የቡና ልማት ውጤታማነት እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

By Tamrat Bishaw

September 09, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና ሲዳማ ክልሎች የቡና ልማት ውጤታማነት እየተሸሻለ መሆኑን የየክልሎቹ አርሶ አደሮችና እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡

በአማራ ክልል አርሶ አደሮች ከቡና ልማት የሚያገኙት ጥቅም እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩት የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ታጀበ ስንሻው ከግብይት ጋር ተያይዞ በተለይም ለውጭ ገበያ ከማቅረብ አኳያ እንቅስቃሴው ደካማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በሲዳማ ክልል አሁን ላይ 161 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና መሸፈኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቀሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 134 ሺህ ሄክታሩ የደረሰና ምርት የሚሰጥ ቡና መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በዘርፉ የተቀናጀ ሥራ በመሰራቱ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ጥራት ያለው ቡና ማቅረብ መቻሉንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘም መሀል ላይ ባሉ ደላሎች የተነሳ አርሶ አደሩ ሲጎዳና መጠቀም ሳይችል መቆየቱን የገለፁት አቶ መስፍን፥ አሁን ላይ ግን አርሶ አደሩ በቀጥታ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ተረካቢዎች የሚያቀርቡበት አሰራር በመመቻቸቱ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮችም ከዚህ ቀደም እምብዛም ውጤታማ እንዳልነበሩ በመግለፅ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ከምርታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሮቹ ተጠቃሚ ለመሆን ያስቻላቸው በዋነኛነት በባለሙያ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ በመስራታቸው መሆኑንም አስረድተዋል።