Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በአንድነት የሚያልፉበት እንደሚሆን እምነታችን ነው- የሀገራት አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በማለፍ ለሰላምና ልማት በአንድነት የሚሰሩበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ፡፡

ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ለኢትዮጵያውያን የመልካም አዲስ ዓመት ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሮቹ በመልዕክታቸው÷ ኢትዮጵያውያን በመጪው አዲስ ዓመት በተባበረ መንፈስ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ሀገርን ለማስቀጠል የሚሰሩበት እንደሚሆን እምነታችን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርክሂን አዲሱ ዓመት ለመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የጤና፣ የብልጽግና፣ የፍቅር እና የደስታ እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን ያገጠሟቸውን ፈተናዎች በብቃት የመወጣት አቅም ያላቸው ህዝቦች ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር በበኩላቸው÷ አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን ያላቸውን መልካም ገጽታና እሴት የሚያስተዋውቁበትን አጋጣሚ እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጋራና በትብብር መንፈስ የተሻለች ሀገር እንዲገነቡ እድል እንሚፈጥርም አመላክተዋል፡፡

“የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ኢትዮጵያውያን አዲስ ተስፋ የሚሰንቁበት ጊዜ ነው” ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የአየር ላንድ አምባሳደር ኒኮላ ብሬናን ናቸው።

ዓመቱ የኢትዮጵያውያን ሰላምና መረጋጋትን እንዲሁም አንድነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበት እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሄይኮ ኒትስሽኬ ÷በአዲሱ ዓመት የተሟላ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማየት ምኞታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በአዲሱ ዓመት ሀገራቸውን በተባባረ ክንድ ወደ ተሻለ ፖቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግሩበት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ÷ አዲሱ ዓመት ለመላ ኢትዮጵውያን የሰላምና የብልጽግና እንዲሆንላቸው የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

Exit mobile version