ኮሮናቫይረስ

በኮሮና ቫይረስ የተጠቁት የላይቤሪያ ባለስልጣን በለይቶ ማቆያ አልቀመጥም በማለታቸው ከስራ ታገዱ

By Meseret Demissu

March 17, 2020

አዲስ አበባ፣መጋቢት 8፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የላይቤያው ፕሬዚዳንት  ጆርጅ ዊሃ  በላይቤሪያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙትን የመጀመሪያውን ሰው ከስራ አገዱ፡፡

ናትናኤል ብላማ የተባሉት እኚህ  ግለሰብ የሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ሃላፊ ሲሆኑ በቅርቡ  ከስዊዘርላንድ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው  ታውቋል፡፡

ይህም በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የመጀመሪያ የቫይረሱ ተጠቂ ያደርጋቸዋል፡፡

ነገር ግን ግለሰቡ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት  በጤና ባለሞያዎች  የሚሰጡት ምክሮች  ተግባራዊ አላደረጉም ተብሏል፡፡

ከዚያም ባለፈ በለይቶ ማቆያ አልቀመጥም ማለታቸው ከስራ  ለመታገዳቸው ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ናትናኤል ብላማ  በበኩላቸው ÷ የጤና ባለሙያዎች የሚመክሩትን ህጉን ተከትዬ እየተገበርኩ ነው በማለት  ክሱ ውድቅ አድርገዋል።

እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናት ለህዝብ የተሳሳተ መረጃ ሰጥተዋል በማለት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር ፕሬዚዳንት ዊሃ ለተከታታይ አንድ  ሳምንት  የዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ የትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የሀገሪቱ ባለሥልጣናትም በፕሬዚዳንቱ የተወሰደው  እርምጃ በቫይረሱ ከተጠቁት ባለስልጣን ጋር በአንድ አውሮፕላን ወደ አገሪቱ የገቡ ሰዎችን ለመከታተል ያስችላል  ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

ምንጭ፡-ቢ.ቢ.ሲ