Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠላቶቻችን አርፈው የሚቀመጡት በሁሉም ዘርፍ ብቃት ላይ መገኘታችንንና ሊያሸንፉን እንደማይችሉ ሲያውቁ ብቻ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠላቶቻችን አርፈው የሚቀመጡት በሁሉም ዘርፍ ብቃት ላይ መገኘታችንን ሲረዱ፣ በስትራቴጂ፣ በቁሳቁስና በቴክኖሎጂ አቅም በልጠው ሊያሸንፉን እንደማይችሉ ሲያውቁ ብቻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ “መከታ” በተሰኘው የመከላከያ ሠራዊት መጽሔት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በጦር ሜዳ ብዙ ጀብዱዎችን የፈጸሙ፣ ጦር ሰብቆና ድንበር ጥሶ የመጣ ጠላትን አንገት አስደፍተው የመለሱ፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለዜጎች ነፃነት መሰዋትን እንደ ክብር የሚቆጥሩ ጀግኖችን አፍርታለች።

ከጥንታውያኑ የግሪክ አፈታሪኮች እስከ ዓድዋው ዘመን የአውሮፓ ጋዜጦች የኢትዮጵያውያን ጀግንነት መወደሱን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ “የዛሬ ዘመን ልጆችም ከአያቶቻችን የወረስነውን ጀግንነት አስጠብቀን ለትውልድ ማውረስ ይጠበቅብናል” ብለዋል።

አሁን ላይ የውጊያ መልክና ቅርጽ መቀየሩን አስታውሰው፥ “እኛ የምንጠቅሰው ሀገራዊ ጀግንነት በእነዚህ መለዋወጦች ምክንያት ምን ያህል እንደተፈተነ በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት አይተናልም” ነው ያሉት።

የእኛ የዝግጁነት መጠን ከዓለም ለውጥ ጋር አብሮ ያለመሄዱ፥ ሀገር እስከማሳጣት የሚያደርስ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ዛሬም ጠላቶቻችን እንደ ድሮው በቀጥታ ውጊያ ሳይገጥሙን የሚያሸንፉበትን መንገድ ከመንደፍ ወደኋላ እንደማይሉ ነው የጠቆሙት፡፡

በድንበር አካባቢ ከሚሰነዝሩብን ቀጥተኛ ጥቃቶች ባለፈ፥ የሽብር ስልጠና የወሰዱ ሰዎችን አስርገው በማስገባት የሚያካሂዱት የሽብር ተግባር ምን ያህል ፈተና ውስጥ እንደሚያስገባን ይታወቃል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ታጣቂዎችንና ያኮረፉ ኃይሎችን ተጠቅመው ሀገራችንን ገዝግዘው ለመጣል ዘወትር እንደቋመጡ መሆኑን ጠቁመው፥ በአንድ በኩል እኛ በምድርና በአየር የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በተጠንቀቅ ስንጠብቅ፥ በሌላ በኩል የሳይበርና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው ፋታ በሚያሳጣ መልኩ ይጎርፋል፤ ይህ እውነታ ዘወትር ነቅተን እንድንጠብቅ ግድ ብሎናል ብለዋል፡፡

ጠላቶቻችንን በስትራቴጂ በልጠን እስካልተገኘን ድረስ ሉዓላዊነታችን በአስተማማኝ መሰረት ላይ አይቆምም ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

በተለይ አሁን የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያለመልሙ አጋጣሚዎች በየአቅጣጫው የተከፈቱበት ወቅት መሆኑንም አንስተዋል።

እኛም ጠላት እንዳይበዛብን ብለን ወደ ከፍታው ከምናደርገው ጉዞ አንገታም ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በአንድ በኩል የህዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቁ ላይ መሆኑ፣ በሌላ በኩል በምግብ ራሳችንን የመቻል እርምጃችን ውጤት ማምጣት መጀመሩ እንዲሁም ቀጠናዊና አህጉራዊ ተጽዕኗችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ “ይቺ ባቄላ ካደረች አትቀቆረጠምም” በሚል ብሂል ተስፋችንን በእንጭጩ ለማስቀረት የሚቋምጡ ኃይሎች በዝተዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው፡፡

አዲስ ዓመት በተበሰረ ቁጥር የኢትዮጵያም ተስፋ እየተበሰረ እንደሆነ እያሰብን መሥራት አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የመከላከያ ሠራዊትም የመጪዋ ኃያል ሀገር የመከላከያ ሠራዊት አባላት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ተስፋ ጠባቂ መሆናቸውን አውቀው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ተስፋ እውን የሚሆነውና ሕልውናዋ በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው መከላከያ “በማንኛውም ጊዜ ለጦርነት ሲዘጋጅ” ብቻ ነው፤ ይህ ሲባል ግን ሠራዊቱ ጠብ አጫሪ ይሆናል ማለት እንዳልሆነም ነው ያብራሩት።

ጠብ አጫሪነት በታሪካችን የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ “ደፍሮ የመጣን ኃይል አሳፍረን እንመልሳለን እንጂ በማን-አለብኝነት በሌላ ሉዓላዊ ግዛት ላይ የኃይል ጥቃት የመሰንዘር ታሪክ አናውቅም” ሲሉም አውስተዋል።

ሠራዊት ለጦርነት የሚዘጋጀው አውዳሚ የሆነ ጦርነትን ለማስቀረት የሚያስችል አቅም ለማዳበር መሆኑንም ገልጸዋል።

ሠራዊቱም “አቅሙን ለማደርጀት ዘወትር መትጋት አለበት” ስንል ሌሎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እያሰብን ሳይሆን ሀገርን ከጠላት ትንኮሳ በብቃት መከላከል እንድንችል በማሰብ ነው ሲሉም ነው ያስረዱት።

“ጠላቶቻችን አርፈው የሚቀመጡት በሁሉም ዘርፍ ብቃት ላይ መገኘታችንን ሲያውቁና በስትራቴጂም ይሁን በቁሳቁስና በቴክኖሎጂ አቅም በልጠው ሊያሸንፉን እንደማይችሉ ሲያውቁ ብቻ ነው” ሲሉም አመላክተዋል::

Exit mobile version