አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንዳንድ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ ዘገባ በኢትዮጵያ ሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል የቀጠለውን ግጭት ይበልጥ እያወሳሰበው መሆኑን ኒውዝላንዳዊው ጋዜጠኛ እና የጂኦፖለቲካ ተንታኝ አልስተር ቶምሰን ገለጸ፡፡
መገናኛ ብዙኃኑ በታቀደ መልኩ በዘገባቸው ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን እንደሚወግኑ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የጠራ መረጃ እንዳይኖረው እንደሚያደርጉ ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበረው ቆይታ አስረድቷል፡፡
በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ደጋፊዎች፣ መሪዎች እና አዛኞች በኩል በመገናኛ ብዙኃኑ የቀጠለው የአሳሳች ዘገባዎች እና መረጃዎች ሥርጭት ዘመቻ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እያሳሳተ እንደሚገኝ እና ለግጭቱ ጥፋተኛ አሸባሪ ቡድኑ እንደሆነ እንኳ እንዳይገነዘብ እንዳደረገም ነው የገለጸው፡፡
ለአብነትም በትግራይ ምንም አይነት ወታደር ባልነበረበት ሁኔታ እንኳን “በትግራይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው” የሚል የትዊተር እና የማኅበራዊ ትሥሥር ገፆች ዘመቻ መካሄዱን አስታውሷል፡፡
በፈረንጆቹ 2021 ሲ ኤን ኤን ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጎን በመሠለፍ “በሱዳን አቅራቢያ ባለ ወንዝ ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን አካላት” ማስመልከቱ እና የተሳሳተ ዘገባ ሠርቶ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሰራጨቱ የታቀደ ፕሮፖጋንዳቸው አንድ አካል መሆኑን ኒውዝላንዳዊው ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን ያስረዳል፡፡
ከዘገባው በኋላ የወጣ መረጃ ግን እንደተባለው ሳይሆን የሰዎቹ አካላት ለረጅም ጊዜ ሳይፈርስ እንዲቆይ በላስቲክ ውስጥ ታጅለው በኬሚካል መታከማቸውን አጋልጧል ብሏል፡፡
3ኛው ዙር ግጭት ከተቀሰቀሰ ሦስት ቀናት በኋላ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ÷ መንግስት መዋዕለ-ሕጻናት የሚገኙ ልጆች ላይ የቦንብ ጥቃት ፈፅሟል በሚል የሐሰት ምስሎች ሲያሰራጩ እውነቱን ለማረጋገጥ ፍላጎት ያሳየ መገናኛ ብዙኃን አለመኖሩንም ነው ጋዜጠኛው የታዘበው፡፡
መረጃው በመጀመሪያ የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረፂዮን በሚኖርበት መኖሪያ አቅራቢያ እንደተፈፀመ ተደርጎ በአሸባሪ ቡድኑ መሰራጨቱንም ነው ያስታወሰው።
በመቀጠል ግን ሁሉንም የትዊተር መረጃዎች እንዳጠፉና የቦንብ ጥቃቱ ሆስፒታል አካባቢ እንደተፈጸመ የሚገልፅ መረጃ እንዳወጡ የተመለከተውን መረጃም ለጣቢያችን አጋርቷል፡፡
ውሸት አሸባሪውን የህወሓት ቡድን የተዋሃደ እና ያለ ውሸት መኖር የማይችል መሆኑን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሊረዱ ይገባልም ነው ያለው፡፡
ቡድኑ ከጎኑ የተሰለፉ እንደ ኬጄቲል ትሮንቮል፣ ማርቲን ፕላውት፣ አሌክስ ደ ዋል፣ ራሺድ አብዲ እና በመሳሰሉ የውሸት ወሬ አሰራጭ ወኪሎች እንደሚጠቀም ይታወቃልም ነው የሚለው።
ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ያለውን መከራ እና የሰዎች ስቃይ ቢያባብስ እንጂ አያረግበውም ነው ያለው፡፡
መገናኛ ብዙኃኑ ከአሸባሪው ወግነው የፈጸማቸውን ወንጀሎች አለማጋለጣቸው በይበልጥ የትግራይን ህዝብ እንደሚጎዳም ነው ያስረዳው፡፡
በተሳሳተ የዓለም አቀፍ ዘገባዎች እና መረጃዎች ምክንያት አሸባሪው ቡድን ጦርነቱን እንዲያቆም ባለመደረጉ አሁንም ቡድኑ የትግራይን ህዝብ እያስገደደ ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ህጻናትን ፊት ለፊት ለጦርነት መማገድ መቀጠሉንም ነው የገለጸው፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ እና ዓለማየሁ ገረመው