አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)መቻቻል፣ መከባባር ፣ መማማርና እውቀት የሰላም ምንጮች ናቸው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ዛሬ ሀገር አቀፍ የሰላም ቀን “ሰላም ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው፡፡
ቀኑን አስመልክቶ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም እንዲሁም ሌሎች የፌደራልና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በሃገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የሰላም ምሰሶ (ፖል) በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ አቁመዋል።
በወቅቱም ÷ መንግስት ጳጉሜን 3 “የሰላም ቀን “ሲል የሰየመው ሰላም ለሰው ልጆች እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።
በመዲናዋ የተለያዩ ያለፍንባቸውንና የከፈልናቸውን መስዋዕትነት የሚያሳዩ ሃውልቶችና በአፍሪካ ሀገራት የተሰየሙ ጎዳናዎች ጭምር መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዛሬ ደግሞ ይህንን የሰላም ሃውልት አቁመናል ብለዋል ፕሬዚዳንቷ።
ሰላም የማይነቃነቅ ወይም የማይጠፋ ሳይሆን ሂደት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ሰላም የምናሳድገውና የምንከባከው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሰላም ጦርነትና የጥይት ድምጽ አለመስማት ማለት አይደለም ፤ይልቁንም መቻቻል ፣መከባባር እንዲሁም መማማርና እውቀት የሰላም ምንጮች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
እነዚህ ሲጠፉም ሰላም ይጠፋል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡