አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሠላማችንን የሚያውኩ ኃይሎችን በተባበረ ክንድ አሸንፈን የሀገራችንን ሰላም እናስጠብቃለን ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
ጳጉሜን 3 የሰላም ቀን በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በአከባበሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሰላም ሰራዊት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ሰላምን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ሰላም ለማስጠበቅ በሚደረገው ርብርብ የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
አያይዘውም “ሰላማችንን የሚያውኩትን ሀይሎች በተባበረ ክንዳችን አሸንፈን የሀገራችንን ሰላም እናስጠብቃለን” ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡