አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያን ድምጽ ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ ላደረጉ የዳያስፖራ አባላት አድናቆታቸውን ገለጹ።
በዋሽንግተን ዲሲ ዙሪያ ካሉና ከሌሎች ግዛቶች በመሰባሰብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫናና የመገናኛ ብዙሃን ዘመቻ በመቃወም በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ድምጻቸውን ላሰሙ የዳያስፖራ አባላት ትልቅ አድናቆት አቅርበዋል ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ።
በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ÷ ”ኢትዮጵያዊ የአንድነት መንፈስን በማጥበቅ በዓለም አደባባይ ድምፅ በመሆናችሁ በእጅጉ እናመሰግናለን ፤ ኮርተንምባችኋልም” ሲሉ አድንቀዋል፡፡
ትናንት ማምሻውን በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ አሸባሪው ህወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
ሰልፉ “በሀገር ሕልውናና አንድነት አንደራደርም!” በሚል መሪ ሀሳብ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት መከናወኑን ነው ኢዜአ የዘገበው።
የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ሰልፉን ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር እንዳዘጋጀውም ተገልጿል።