አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ብትገኝም ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ያለውን የሰው ኃይል በክኅሎት ለማደርጀት የተለያዩ ተግባራትን በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ የማካተት ሥራ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናዎቹ ሀገር ወዳድነትን ከታታሪነት ጋር ያስተሳሰሩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፥ እስከ 2 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች በአጫጭር እና በመደበኛ ሥልጠናዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የገለጹት።
የውጭ ሀገራት የሥራ ሥምሪትን በተመለከተ ላለፉት ወራት ከሥልጠና ጀምሮ እስከ ሥምሪት ያለውን ሥርዓት በመፈተሽ አሰራሩን ለመቀየር መሞከሩንም ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ሂደት 28 የሚሆኑ ደረጃዎችን ያልፍ እንደነበረና አሁን ላይ ግን ወደ 14 ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፥ በቀጣይ ከ14 የሂደት ደረጃዎች ዝቅ ለማድረግ እንደሚሰራም ነው ያመላከቱት፡፡
እንግልቱ በጣም ሰፊ እና ዜጎችን የሚያጉላላ ብሎም ለአላስፈላጊ ወጪ እና ህጋዊ ላልሆኑ ደላላዎች የሚዳርግ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
የውጭ ሀገር ሥምሪት አገልግሎት መስጫ ማዕከሎችን የማሥፋት ሥራም እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ለውጪ ሀገር ሥምሪት አዲስ የተገነባ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በቅርብ ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ወደ ውጪ ሀገር የሚሠማሩ ዜጎች በቂ የሥነ-ልቦና ዝግጅት እንዲሁም ስለሚሰማሩበት ሀገር ዕውቀት እና ክኅሎት እንዲኖራቸው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት አዲስ ሥርዓተ-ትምህርት እንዲያዘጋጁ እና እንዲከልሱ መደረጉንም ነው ያነሱት።
የሥራና ክኅሎት ጉዳይ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ተግባር እንዳልሆነና ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡