የሀገር ውስጥ ዜና

“ኢትዮጵያ ለሰላም ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርጋለች” – አልስተር ቶምሰን

By Alemayehu Geremew

September 06, 2022

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ማድረግ የሚችለውን ሁሉ መወጣቱን በኒውዚላንድ ለ“ስኩፕ” ሚዲያ የሚሠራው ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን ገለጸ።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ችግር በውይይት ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ያላትን ጥልቅ ፍላጎት ዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ በማሳተፍ ጭምር ማረጋገጧን አልስተር ቶምሰን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለማደራደር የጀመረውን ጥረትም አሸባሪው የህወሓት ቡድን ማጨናገፉን አስረድቷል፡፡

የአሸባሪው የህወሓት ቡድን የየአፍሪካ ኅብረትን ጥረት ከረገጠ በኋላም እንደገና ወደ ጦርነት መግባቱን ነው የጠቆመው፡፡

እንደ አልስተር ቶምሰን ÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን እስካሁን ያለፈበት ሂደት የሚያመላክተው ሰላማዊ ድርድርን እንደማይፈልግ ነው፡፡

በርካታ ዓለምአቀፍ የሰላም አደራዳሪ ልዑካን አንዴ አዲስ አበባ፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ መቀሌ እየተመላለሱ ሊያደራድሩት ቢሞክሩም አሸባሪ ቡድኑ በየጊዜው ቅድመ ሁኔታዎችን እየደረደረ ወራት ማስቆጠሩንም ነው ያስታወሰው፡፡

የዓለም አቀፉ የሰላም አደራዳሪ ልዑካን አባላት ከአሸባሪው ቡድን ጋር ፎቶ ሲነሱ መስተዋላቸውም ነገሩን በአንክሮ እንዳልተመለከቱት የሚጠቁም መሆኑን ነው ጋዜጠኛው የገለጸው፡፡

ጋዜጠኛ እና ተንታኙ አልስተር ቶምሰን÷ በአዲስ አበባ የተቋቋመው ዐቢይ የሰላም ኮሚቴ መንግስት ለሰላም ያለውን ፍላጎት የሚያረጋግጥ ነውም ብሏል፡፡

የአሁኑ ግጭት ከመቀስቀሱ በፊትም የኢትዮጵያ መንግስት ሁለት ጊዜ የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ እንደወሰደ ገልጾ፥ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ግን ለዚህ እርምጃው እውቅና ለመስጠት ፍላጎት እንዳላሳየም አብራርቷል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ቢቀርብለትም በአሸባሪ ቡድኑ ደንቃራ በመሆኑ ጥረቱ እንዳልተሳካ ተናግሯል፡፡

ይልቁንም አሸባሪው ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች በተደጋጋሚ ወረራ እንደፈጸመ እና ተመትቶ እንደተመለሰ ነው አልስተር ያስታወሰው፡፡

አሸባሪው ቡድን ወረራ ባካሄደባቸው አካባቢዎች ሁሉ ንጹሐንን መጨፍጨፉንም ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ላሳየው ትዕግስት እና ጥረት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና መስጠት አለበት ሲልም ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን በአጽንኦት ጠይቋል፡፡

በወንደሰን አረጋኸኝ እና ዓለማየሁ ገረመው