አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት ግጭትን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት እንደሌለው አፈትልኮ የወጣው የራሱ ሰነድ አረጋገጠ።
የሽብር ቡድኑ “የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” በሚል ያዘጋጀው ሰነድ አፈትልኮ ወጥቶበታል።
ሰነዱ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ የረገጠ እና ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ንቀት ያሳየበት ነው፡፡
“በጦርነት ሂደት ውስጥ የመረጃ ልዕልና ለማግኘት እና በርካታ ሃይሎችን ከጎንህ ለማሰለፍ ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለህ አስመስለህ እራስህን ማቅረብ መሆኑ ሊረሳ አይገባም” ሲል ሰነዱ ህወሓት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በግልጽ መዋሸቱንና ማጭበርበሩን አጋልጧል፡፡
መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ብሎ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲሄድ ቁርጠኝነቱን ቢያረጋግጥም፥ በአንጻሩ የሽብር ቡድኑ “የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የጀመረው አካሄድ በፍፁም የማያዋጣ ነው” ነው ሲል በማጣጣል ሰላማዊ መፍትሔን አለመቀበሉን ሚስጥራዊ ሰነዱ አሳይቷል፡፡
“የትግራይ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በመንግሥት የሰላም አማራጭ ሳይሆን ‘በክንዳችን ብቻ መሆኑን በፅኑ እናምናለን’ ” በሚል ዕብሪታዊ አካሄድ የትግራይን ሕጻናት እና ወጣቶች ወደ ጦር መማገዱን ሰነዱ አመላክቷል፡፡
አፈትልኮ የወጣው የአሸባሪው ህወሓት ሰነድ እንዳመላከተው፥ ለትግራይ ሕዝብ ያዘነ በመምሰል የትግራይ ሕዝብ ነጻ እንዲወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት መወገድ አለበት ይላል፡፡
የሰላም አማራጭን ረግጦ ለሚነዛው ሽብርም ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ አጋር እንዳለው ሰነዱ አመላክቷል፡፡
“የውስጥ ትግላችንን በማገዝ የሚንቀሳቀሱ እንደ ኦነግ የመሳሰሉ አጋሮቻችን እንዲሁም በተለያየ የዓለም ማዕዘናት የሚገኙ የትግራይ ዳያስፖራና ዓለም አቀፍ አጋዦቻችን በዚህ ጊዜ የተሳካ ጥምረት በማድረግ ወደ አዲስ አበባ በምናደርገው እንቅስቃሴ ከጎናችን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን የክልላችን ዋና ስራ አስፈፃሚ በዝግ ባደረገው ውይይት አረጋግጧል” ብሏል ሰነዱ፡፡
ምስጢራዊ ሰነዱ፥ የሽብር ቡድኑ ውስጣዊ አቅሙን በማጠናከር በርካታ ወጣቶችን ወደ ጦር ግንባር በመላክ ሀገር የማፍረስ ተግባሩን እንደሚቀጥልበት ያመላክታል፡፡
“የትግራይ ወጣቶችን አሁን የሚደረገው ትግል ወደ አዲስ አበባ የመጨረሻ ምዕራፍ ትግላችን እንደሆነ በማሳመን የህወሓት አመራር ካለፈው ዘመቻ ራሱን ገምግሞ የነበሩበትን ክፍተቶች በሙሉ በመዝጋት ለመንቀሳቀስ ቆርጦ መነሳቱንና የትግራይን ሕዝብ ለማሳመን የሚያስችል የሚዲያ ሥራ እየተሰራ ይገኛል” ይላል።
“የመሳሪያና ትጥቅ አቅም አለማጠናከር ባለፉት ዘመቻዎች የነበረብን ክፍተት እንደሆነ ተገምግሟል” ያለው ሰነዱ፥ ይህንን ግምገማ በማየት በውጭ ያሉ አጋዦቻችን በአስቸጋሪ እና አጣብቂኝ ጊዜ ውስጥም ቢሆን ችግሩን አልፈው ዘመናዊ ትጥቆች እንድንታጠቅ አድርገውናል” ሲል ሰነዱ ምን ያህል ህወሓት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አሰይቷል።
“የዚህ ዘመቻ ምዕራፍ መራርና በርካታ መስዋእትነት የሚጠይቅ በመሆኑ አሁንም ዘመናዊ ትጥቅ ለመከላከያ ሃይላችን እንዲያቀርቡልን የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከውስጥና ከውጪ ተባባሪዎቻችን ጋር ያለንን ስራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል” በሚል ያስቀመጠው ሃሳብም የቡድኑን ከሰላማዊ መፍትሄ ይልቅ ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንን ነው፡፡
በአጠቃላይ አሸባሪው ህወሓት ከላይ ከላይ ሰላም ሰላም ሲል ቢታይም፥ ቡድኑ ግን የሰላም የሰላም ዲስኩሩን ለጦርነት ለመዘጋጀት በማዘናጊያነት ሲጠቀም እንደነበር ሰነዱ በግልፅ አሳይቷል።
“በትግራይ የሚገኙ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሰብአዊ ድጋፍ ማከማቻ መጋዘኖች ፋሽስቱን ለማስወገድ በምናደርገው ትግል የስንቅ አቅርቦት እንዳይጓደል በቁጥጥራችን ስር ልናደርጋቸው ይገባል” ሲል ያስቀመጠው ሀሳብም ለተጎጂ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የመገባን የእርዳታ እህልን ለጦርነት ዓላማው ያለሀፍረት በመጠቀም ላይ እንደሚገኝ የሚያጋልጥ ነው።
“ከአለም አቀፍ የእርዳታ አስተባባሪዎች አወንታዊ የሆነ ግንኙነቶች በማጠናከር ረሃብና ተረጅነት ከሕዝባችን ትክሻ ላይ ለማውረድ ለምናደርገው ትግል ደጋፊ እንዲሆኑና ከጎናችን እንዲቆሙ ልናደርግ ይገባል” ሲል ዓለም አቀፍ የረድእት ድርጅቶች የሽብር ቡድኑን ህገወጥ ድርጊት እንዲሸፍኑለት እንደሚሰራ የሚያሳይ ሆኗል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!