አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት ባላፉት አራት አስርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ሁሉን አቀፍ ግፍ የሚያሳይ የጥናት ውጤት በመጽሃፍ መልክ ለህዝብ ይፋ ሆነ።
በምረቃ መርሐ ግሩ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ር ዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
ዶክተር አስራት አጸደወይን፥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እውነትን የመፈለግ፣ዕውቀትን የማስረፅና ሰንዶ ለማህበረሰብ የማድረስ ሚና ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርስቲ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ላይ አሰቃቂ የሆነ መዋቅራዊ የዘር ማጥፋት ማካሄዱን ዩኒቨርሲቲው 21 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን አቋቁሞ ለ18 ወራት ሳይንሳዊ ጥናት አድርጓል ብለዋል።
ችግሮችን ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በቂ እውቀት ሊኖር ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ የምርምር ውጤት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የተፈፀመውን ዘግናኝ ግፍ ለዓለም ማህበረሰብ ሚያሳይ ነውም ብለዋል።
መጽሃፉ “ወረራና መዋቅራዊ የዘር ማጥፋት በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን፥ በሰባት ምእራፎች 380 ገጾች አሉት።
በዘር ፍጅት፣ ፆታዊ ጥቃት፣ የታሪክና ማንነት ወረራና ኢኮኖሚያዊ ምዝበራ፣ በጤና እና ትምህርት ላይ የተፈፀሙ ግፎች እና ሌሎችም ዘርፎችም ላይ በጥልቀት መረጃዎች የተሰባሰቡበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታቸው ጀምበር በበኩላቸው፥ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አካባቢ በአሸባሪው ቡድን የተፈጸመው ግፍ ቆሞ የሚመሰክር መሆኑን አንስተዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑና በሽፍትና ዘመኑ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አካባቢ ወጣቶች ያለመካሪ አባቶች፣ ያላሳዳጊ እንዲቀሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በሹመት አለማዩሁ