Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሌላኛው የህልውና የፍልሚያ ግንባር የግብርና ልማት ነው – አማራ ክልል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሌላኛው የህልውና የፍልሚያ ግንባር የግብርና ልማት ነው ሲል የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው እንዳለው ፥ ሸብርተኛው የህወሓት ቡድን የክረምት ወራትን እየጠበቀ ለሦስተኛ ጊዜ ወረራ ፈፅሟል ፤ ይህን ወቅት የሚመርጠው የግብርና ዘርፉን ሆን ብሎ ለማዳከም ጭምር ነው ብሏል።

አርሶ አደሩን ከግብርና ስራው አስተጓጉሎ አማራን እንደ ህዝብ ለማስራብ እና ህልውናውን ለማጥፋት፤ ኢትዮጵያን ደግሞ እንደ ሀገር በኢኮኖሚ ደካማ አድርጎ ራሷን መከላከል እንዳትችል በማድረግ ሀገሪቱን ለማፍረስ አስቦ የፈፀመው ጥቃት እንደሆነም ነው ያመለከተው።

“የተከፈተብንን ጦርነት በጀግንነት እየመከትን የግብርና ስራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲልም ገልጿል፡፡

ሌላኛው የህልውና የፍልሚያ ግንባር የግብርና ልማት መሆኑንም ነው የክልሉ ግብርና ቢሮው ያነሳው፡፡

በዚሁ ግንባር የተሰለፋችሁ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና መላው አርሶ አደሮች በእልህና በቁጭት ያለንን አቅም ሁሉ ተጠቅመን በሰብል ጥበቃ በተለይ አረም ማረምና ተባይ አሰሳ ማድረግ፣ የተተከሉ ችግኞች መንከባከብ፣ በቀሪ እርጥበት ለሚዘሩ ሰብሎች ትኩረት መስጠት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ኮምፖስት ዝግጅት አጠናክሮ መቀጠል፣ ለቀጣይ ዓመት መስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅት ማድረግና ሌሎች ስራዎች ላይም ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ አለብን ብሏል።

“ምንጊዜም ቢሆን ፈተና ውስጥ ብንሆን፤ ችግር ቢያጋጥመን፤ ጦርነት ቢታወጅብን በጀግንነት እየተፋለምን ፤በፅናት እየመከትን ከግብርና ስራችን ለአፍታም ቢሆን አይናችንን አንነቅልም” ማለቱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version