የሀገር ውስጥ ዜና

የቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት ለ2 ሺህ አይነስውራን የማንበቢያ መነፅር አበረከተ

By Amele Demsew

September 03, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ለ2 ሺህ አይነስውራን “ኦርካም ማይ አይ” የተሰኘ ዘመናዊ የማንበቢያ መነፅር አበረከተ።

መነጽሩ አማርኛም ሆነ እንግሊዝኛ ለማንበብ የሚረዳ ሲሆን፥ የገንዘብ ኖቶችን እና ቀለም ለመለየት እና ከፊት ለፊት ምን እንዳለ እና ማን እንደመጣ መዝግቦ በመያዝ መረጃ እንደሚሰጥ ተገልጿል ፡፡

ከለጋሾች በተገኘ ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ የገባዉ የማንበቢያ መነጸሩ፥ የሰው እገዛን በመቀነስ አይነስውራኑን ህይወት የሚቀይር ነው ተብሎለታል፡፡

መነፅሩ ከአንድ አመት በፊት በ150 አይነስውራን በፓይለት ፕሮጀክት ተሞክሮ ለአይነስውራኑ እጅግ የጠቀመ ሆኖ በመገኘቱ አሁን 2 ሺህ ሰዎችን በሚጠቅም መልኩ አማርኛ እንዲያነብና የድምጽ ትእዛዝን እንዲቀበል ሆኖ የተሰራ ነው ተብሏል፡፡

መነጽሩ በአዲስ አበባ በሀዋሳ እና አካባቢዉ እንዲሁም በጎንደር ተደራሽ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፥ 35 በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ ስለአጠቃቀሙ ስልጠና መሰጠቱን ከቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡