የሀገር ውስጥ ዜና

በሀገር ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመቀልበስ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አረጋገጡ

By Amele Demsew

September 03, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ ) “በሀገር ሉዓላዊነትና በህዝባችን ሰላም ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመቀልበስ የሚጠበቅብንን ሁሉ ድጋፍና ርብብር እናደርጋለን” ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባለታ አረጋገጡ፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር በሀገሪቱ ካዋዙሉናታል ፕሮቪንስ፣ ፒተርማርዝበርግ ከተማና በአካባቢው ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባለት ጋር በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በመድረኩ አምባሳደሩ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን፥ የኢፌዴሪ መንግስት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዳቸውን ተጨባጭ የሰላም አማራጭ፣ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን በመጣስ በአጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ዳግም ወረራ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መንግስት ተገዶ ወደ መከላከል እርምጃ እንደገባ አምባሳደሩ ማብራራታቸውን ከደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በተለያዩ ጊዜያት ለቀረቡት አገራዊ ጥሪዎች ምላሾችን በመስጠት የሚታወቅ መሆኑን አውስተዋል። በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ በተባባረ ክንድ ለመቀልበስ በሚደረገው ተጋድሎ ማህበረሰቡ ህዝባዊ ደጀንነቱን ዳግም እንዲያረጋግጥ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው÷ በአገር ጉዳይ ላይ እንደማይደራደሩ ገልጸው በአሁኑ ወቅትም በአገርና በህዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እየተደረገ ላለው ተጋድሎ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።