Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በትራምፕ የግል መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ11 ሺህ በላይ የመንግሥት ሰነዶች ተገኙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍሎሪዳ በሚገኘው የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ11 ሺህ በላይ የመንግሥት ሰነዶች በሕገ ወጥ መንገድ ተወስደው መገኘታቸው ተገለጸ፡፡
የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) በፈረንጆቹ አቆጣጠር ባለፈው ነሐሴ 8 ፍሎሪዳ በሚገኘው በዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት ላይ ባደረገው ፍተሻ ከ11 ሺ በላይ የመንግሥት ሰነዶችን እና ፎቶግራፎችን እንዲሁም 48 “ምሥጢር” የሚል ምልክት የተፃፈባቸው “ማህደሮች” ማግኘቱን ትናንት ይፋ አድርጓል።
የፌዴራል የምርመራ ቢሮ በዶናልድ ትራፕ ላይ ባካሄደው የምርመራ ውጤት መሠረት፥ ከትራምፕ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ምስሥጢር የያዙ፥ ማንም ሊያገኛቸው ያልተፈቀዱና በሕግ ከተፈቀደው ቦታ ውጪ መቀመጥ የሌለባቸው ሰነዶችን ከነጩ ቤተ መንግሥት ማስወገዳቸውን እና በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ግል መኖሪያቸው መውሰዳቸውን አረጋግጧል።
በዩናይትድ ስቴትስ የወረዳ ዳኛ የሆኑት አይሊን ካኖን በትራምፕ ጠበቆች እና በፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዓቃብያነ ሕግ መካከል ማህተም በሌላቸው ሰነዶች ዙሪያ ትናንት የቃል ክርክር አካሂደዋል፡፡
ዳኛው ክርክሩን ካዳመጡ ከአንድ ቀን በኋላ በትራምፕ መኖሪያ ቤትውስጥ የተገኙትን ቁሳቁሶች በትራምፕ ጥያቄ መሰረት ልዩ ግምገማ ለማካሄድ ባለሙያ መሾም ይኖርባቸው እንደሆነ ማጤናቸው ነው የተመላከተው።
ዳኛው ልዩ ባለሙያ ለመሾም አሊያም ላለመሾም ወዲያውኑ ብይን ለመስጠት ቢዘገዩም፥ ነገር ግን በፍትህ ሚኒስቴር የቀረቡ ሁለት መዝገቦችን ለመክፈት እንደሚስማሙ ተናግረዋል።
“ኤፍ ቢ አይ በሰነዶቹ ዙሪያ የምርመራ ሥራ እያከናወነ እስከሆነ ድረስ፥ ልዩ ባለሙያ መሾም ጊዜ ማባከን ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ በትራምፕ ተሹመው የነበሩት የቀድሞ የአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የፌዴራሉ ቢሮ መርማሪዎች በፈረንጆቹ ጥር 2021 ከትራምፕ መኖሪያ ቤት ውስጥ ባገኟቸው 15 ሳጥኖች ውሰጥ ያሉትን መረጃዎች ፈትሸው የምሥጢር ምልክቶች የተደረጉባቸው 184 ልዩ ሰነዶችን አግኝተዋል።
ከነዚህም መካከል 67 ሰነዶች “ለማየት የተከለከሉ” ፣ 92 ሰነዶች “ምሥጢር” ፣ 25 ሰነዶች ደግሞ “ ከፍተኛ ምሥጢር” የሚል የጽሑፍ ምልክት የተጻፈባቸው መሆናቸው ይፋ ሆኗል።
ከሳጥኖቹ መካከል የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የእጅ ጽሑፍ ያለባቸው እንደሚገኙም ማንነቱ ያልተገለጸ፥ ነገር ግን በተዘጋጀው የምርመራ የቃለ መሐላ ሰነድ ላይ ፊርማው እንደሚገኝ አንድ የፌዴራል ቢሮ መርማሪ መናገሩንም በወቅቱ ሮይተርስ መዘገቡ ይታወሳል።
ዶናልድ ትራምፕ ስለጉዳዩ በሰጡት አስተያየት፥ የሰነዶቹ መገኘትም ሆነ የምርመራ ሂደቱ በአጠቃላይ ጊዜ ከማባከን ውጪ ምንም ፋይዳ የማይገኝባቸው ናቸው ሲሉ የክስ ሂደቱን አጣጥለውታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version