Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ህወሓት ከሽብር ተግባሩ ታቅቦ ወደ ሰላም መድረክ እንዲመለስ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ሊያደርግ ይገባል – አምባሳደር ጀማል በከር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እና የሰብዓዊ ድርጅቶች የሽብር ቡድኑ ከሽብር ተግባሩ እንዲታቀብ እና ወደ የሰላም መድረክ እንዲመጣ ግፊት ሊያደርጉ እንደሚገባ በፓኪስታን የኢፌዴሪ አምባሳደር ጀማል በከር ገለጹ፡፡
አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን ቴሌቭዥን ጣቢያ ፒ ቲቪ(PTV) ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በፓኪስታን በደረሰው የጎርፍ አደጋ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የአየር ጸባይ ለውጥ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እና የሰብዓዊ ድርጅቶች የሽብር ቡድኑ ከሽብር ተግባሩ እንዲታቀብ እና በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ወደ ሚደረገው የሰላም የውይይት መድረክ እንዲመጣ ግፊት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አምባሳደሩ አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
መንግስት የሀገሪቱን ደህንነት፣ ሉዓላዊነት እና የህዝቦቹን ደህንነት የማስጠበቅ ሙሉ ህገ-መንግስታዊ መብትና ስልጣን አለው ነው ያሉት አምባሳደሩ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጦርነቱን በፍጹም አይፈልጉትም ያሉት አምባሳደር ጀማል መንግስት በሽብር ቡድኑ የተከፈተውን ጦርነት ለማስቀረት እና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን እና አሁንም እያደረገ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የህወሓት የሽብር ቡድን በትግራይ ክልል በፈጠረው ችግር ምክንያት የተስተጓጎሉ መሰረተ ልማቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ መንግስት ጥረት ቢያደርግም በቡድኑ የሽብር ተግባር ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል ነው ያሉት፡፡
አምባሳደሩ በፓኪስታን በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክንያት በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን በራሳቸው እና በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ስም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version