አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በየትኛውም ቦታ የሚገኝ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ መንግስት እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት አሸባሪውን ህወሓት ጥቃት በመመከት እየተወጡት ያለውን የሞራል እና ህጋዊ ግዴታ እንዲደግፍ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ተሟጋች ጥምረት ጥሪ አቀረበ።
በአውሮፓ ሀገራት፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳ የሚገኙ 16 የኢትዮጵያውያን ማህበራትን የያዘው ጥምረቱ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም፥ የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ክልል የሚደረግ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲሳለጥ በማሰብ የተናጥል የተኩስ አቁም ማድረጉ ያስገኘውን ጠቀሜታ ዘርዝሯል።
መንግስት ይህን በማድረጉ ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ ማስቻሉን ነው ጥምረቱ ያመላከተው።
ሆኖም ህወሓት የፌደራል መንግስት ባደረገው ልክ ለተኩስ አቁም መገዛት ሲገባው በተቃራኒው የሰብዓዊ አቅርቦትን ለወታደራዊ እንቅስቃሴው ማዋሉን አብራርቷል።
ለአብነትም በቅርቡ መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉን ነው የጠቀሰው።
ህወሓት ህፃናትን በግድ ለጦርነት በመመልመል እና የህዝብ ማዕበልን በመጠቀም ዜጎችን እየማገዱ መሆኑን ጥምረቱ አውግዟል።
አንድ ቤተሰብ እርዳታን ለማግኘት ቢያንስ አንድ ሰው ለጦርነቱ እንዲያዋጣ በማስገደድም እየፈፀመ ያለውን የጦር ወንጀል እንደሚቃወም ነው ጥምረቱ በመግለጫው ያስታወቀው።
ጥምረቱ÷የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜኑን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሄደበትን መንገድ አድንቋል፡፡
በአንጻሩ የህወሓት ጠብ አጫሪ ድርጊት በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም መጥፋት ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍሪካ ህብረት የተጀመረው የሰላም ጥረት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ጥረቱን እንዲደግፍ ጠይቋል።
ህወሓት ወደ ሰላም ውይይት እንዲመጣም ግፊት እንዲያደርጉ ነው ያሳሰበው።
ጥምረቱ የኢትዮጵያ መንግስት ለግጭቱ ሰላማዊ እልባት ለመስጠት እና የሀገሪቱን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እያከናወነ ያለውን ተግባር እንደሚደግፈም አረጋግጧል።